የእሁድ እይታዎች

የላቀ ስኬት ራሱን የመግለጥ ተፈጥሮ አለው። በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ውጤት የዓለምን ትኩረት ስቧል።

‎በቅርቡ የአፍሪካ ኅብረት ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና የዲጂታል ጤና ሻምፒዮን አድርጎ መሾሙ፣ ቀደም ሲል የተቀበሏቸው የአለም የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) ሽልማት፣ የአግሪኮላ ሜዳሊያ፣ የላቀ የአፍሪካ መሪነት ሽልማት እና የኢጋድ (IGAD) የቱሪዝም ሻምፒዮንነት እውቅናዎች ላይ የተጨመረ ማረጋገጫ ነው።
‎እነዚህ የክብር እና የአፈጻጸም እውቅናዎች የግል ስኬቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ ኢትዮጵያ በቁልፍ ዘርፎች እያሳየች ያለችውን ከፍ እያለ የመጣ የመሪነት ሚና የሚያረጋግጡ ናቸው።

‎የአፍሪካ ኅብረት ሹመት በዲጂታል ፈጠራ የታገዘውን ሰፊ ሀገራዊ ትራንስፎርሜሽን የሚያንጸባርቅ ነው። ኢትዮጵያን “ዘግይቶ ከመድረስ ዕዳ ወደ ቀድሞ መድረስ በረከት” ለማሸጋገር በተቀመጠው ርዕይ መሠረት፣ ሀገሪቱ በፈጠራ እና ቴክኖሎጂዎች ግንባር ቀደም ለመሆን ደፋር እርምጃዎችን ወስዳለች።

‎የአፍሪካ የመጀመሪያውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት የመሰረተችው ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ የመጀመሪያውን፣ በዓለም ደግሞ ሁለተኛ የሆነውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲም በመገንባት ላይ ትገኛለች።

‎በተመሳሳይ በዲጂታል መሠረተ ልማት፣ በበይነ መረብ የመንግሥት አገልግሎት (e-government) እና በፈጠራ ሥነ-ምህዳር ላይ እየተደረጉ ያሉ ኢንቨስትመንቶች ተጨባጭ ውጤቶችን እያስገኙ ይገኛል።
‎በአሁኑ ወቅት ከ132 በላይ ተቋማት በፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓት ስር ተሳስረዋል። በ31 የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች አማካኝነትም ከ476 ተቋማት የሚገኙ 2,396 አገልግሎቶች ለሕዝብ ተደራሽ ሆነዋል። ይህም ቢሮክራሲያዊ እንቅፋቶችን በእጅጉ ቀንሷል። ከ41 ሚሊዮን በላይ የፋይዳ መታወቂያ ተጠቃሚዎች እና 58 ሚልዮን የሞባይል ገንዘብ ደንበኞች መኖራቸው የጥሬ ገንዘብና በአካል በመገኘት የሚከናወኑ የአሠራር ችግሮችን እየቀረፉ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ራሷን ከመለወጥ ባለፈ፣ የ2030 የዲጂታል ግቦችን ለማሳካት ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ የአፍሪካን ዲጂታል ዘርፍ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመቅረጽ ላይ ትገኛለች።

‎ርዕይን ፈጽሞ በመገኘት ጉልህ ዐሻራን እያሳረፈ የሚገኘው የአመራር ቁርጠኝነት ከቴክኖሎጂ ባሻገር፣ በአካባቢ ጥበቃ ረገድም ግልጽ ውጤት አሳይቷል። በ2011 የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ፣ ኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን በማስተባበር የደን ጭፍጨፋን እና የአፈር መሸርሸርን መግታት ችላለች። በዚህም በስድስት ዓመታት ውስጥ የደን ሽፋኗን ወደ 23% አሳድጋለች። በፖሊሲ ተደግፎ የተጀመረው ይህ ንቅናቄ ወደ ሀገራዊ ባህል በመሸጋገሩ ለወጣቶችና ለሴቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ሥነ-ምህዳርን በማደስና የአካባቢ ጥበቃን ከሀገራዊ ጸጋ ጋር በማስተሳሰር ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ለዚህም እውቅና ይሆን ዘንድ፣ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ለዘላቂ የደን ልማት የ2025 የስኬት ሽልማት አበርክቶላቸዋል።

‎ከ2011 ጀምሮ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች በመተከላቸው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለሰፊ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ የአኅጉሩ ተምሳሌት ሆናለች።
‎ይህ ስኬት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ተሟጋችነት ያላትን ሚና ከተሳታፊነት ወደ መሪነት ቀይሮታል። ሀገራችን አሁን ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ውይይቶችን የምታስተናግድና የምትመራ ሲሆን፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ከኢኮኖሚ ጥንካሬ፣ ከምግብ ዋስትና እና ከሀገራዊ አንድነት ጋር እንዴት እንደሚጣጣም በተግባር እያሳየች ነው።
‎የዜጎች ተጠቃሚነትን በተመለከተ፤ የውኃ ተፋሰሶች መታደስ፣ የምግብ ሥርዓት መረጋጋት እና የአረንጓዴ የሥራ ዕድሎች መስፋፋት ተጨባጭ ጥቅሞች እየሰጡ ለመቀጠላቸው በርካታ አብነቶች አሉ።

‎የኢትዮጵያ ለውጥ ቱሪዝምንና የከተማ ማደስ ሥራዎችንም ይጨምራል። በ2017 በኢጋድ የቱሪዝም ሻምፒዮን ተብለው የተመረጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ የተፈጥሮ ቱሪዝምን፣ የከተማ ውበትንና የመሠረተ ልማት ዝርጋታን አፋጥነዋል። ቱሪዝም አሁን ላይ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ከተሞችን በማነቃቃትና ኢትዮጵያንና የአፍሪካ ቀንድን ተመራጭ የዓለም የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ረገድ የዕድገትና የቀጣናዊ ትስስር ሞተር ሆኗል።

‎በግብርናው ዘርፍም የተመዘገቡት ውጤቶች ጉልህ ድርሻ ይዘዋል። በጥር 2016 ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግብርናውን ዘርፍ በመለወጣቸው ከዓለም አቀፉ የእርሻ እና የምግብ ድርጅት ከፍተኛውን ክብር የአግሪኮላ ሜዳሊያ ተቀብለዋል። በ”ስንዴ ለምግብ ሉዓላዊነት” መርሃ ግብር አማካኝነት የእርሻ መሬት የሰፋ ሲሆን፣ ዓመታዊ የስንዴ ምርት በ2010 ከነበረበት 27 ሚሊዮን ኩንታል በ2017 ወደ 280 ሚሊዮን ኩንታል አድጓል። ይህ ለውጥ ከውጭ የሚገባ ምርትን ከመቀነሱም በላይ የገበሬውን ገቢ በመጨመር ኢትዮጵያ በስንዴ ራሷን እንድትችል አድርጓል።

እነዚህ እውቅናዎች የኢትዮጵያን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤታማነት የሚያረጋግጡ፣ ሀገሪቱን ለአኅጉራዊ የግብርና ትራንስፎርሜሽን እና ለምግብ ሉዓላዊነት ዓርአያ ያደረጉ ናቸው።
‎በዲጂታል ፈጠራ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በቱሪዝም እና በግብርና የታየው አንድ ግልጽ እውነታ፤ በጠንካራ አፈጻጸም የታገዘ ርዕይ መኖሩ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አመራር ታላቅ ዓላማ ከተግባር ጋር ሲዋሃድ እውቅና እና ሽልማት ተከትሎ እንደሚመጣ ያሳያል። እውቅናው በራሱ ግብ ሳይሆን፣ የተመዘገበው እውነተኛና ሊለካ የሚችል ለውጥ ማረጋገጫ ነው።

‎‎እነዚህ ስኬቶች ከሽልማት በላይ፣ አንድን ሕዝብ ከፍ የሚያደርጉና የሀገሪቱን የወደፊት የዕድገት አቅጣጫ የሚቀርጹ ዘላቂ መሠረቶች ናቸው!

PMOEthiopia

ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication

Similar Posts