የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ስኬቶች እና የንፁህ ኢነርጂ ተስፋዎች
ሚያዝያ 19/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎችን በማነቃቃት ረገድ ለንጽህ ኢነርጂ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ በተለይም የኢንቨስትመንት ገጽታን በአዲስ መልክ በመቀየር ዘላቂ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እድገት እንዲገነባ እያደረገ ነዉ፡፡
ባለፉት ሰባት ዓመታት የኢንዱስትሪ መስፋፋት ኢኮኖሚውን ከማንሰራራት ባለፈ ከፍተኛ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ስቧል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ለንፁህ ኢነርጂ ያላት ቁርጠኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሆኑ ለኢንቨስትመንት መነቃቃት ሰፊ እድሎች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡
የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች፣ የንፋስ ሀይል እና የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች ኢትዮጵያን በታዳሽ ኢነርጂ ዘርፍ የቀጠናዉ ማዕከል እንዲትሆን አስችሏታል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (GERD) ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ለኢንዱስትሪ የኃይል ማመንጫ ለመጠቀም ያላትን አቅም በተጨባጭ ያረጋገጠ ነዉ፡፡
የንፁህ ኢነርጂ አቅም መገንባት በነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት እንዲቀንስ ከማድረጉም ባሻገር የምርት ወጪዎችን በእጅጉ ይቀንሳል፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ እና የኤክስፖርት ዘርፎች ተወዳዳሪነትን ያሳድጋል፡፡ ይህም በዘርፊ የተሰማሩ ባለሀብቶች በታዳሽ ምንጮች ዋስትና ያለዉና የኢነርጂ ደህንነቱ በዘላቂነት የተረጋገጠ ኢንዱስትሪዎች እንዲገነቡ ያስችላል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ስኬቶች ከጨርቃጨርቅ እና ከቆዳ ማምረቻ እስከ አግሮ ፕሮሰሲንግ ከተፈጠሩ የኢነርጂ አብዮት ጋር የተሳሰሩ ናቸው፡፡ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑና በስፋት ምርት እንዲያመርቱ፣ እንዲሁም ለዜጎች የሥራ እድሎችን እንዲያሳድጉ ያስችላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዕድገት ያላት ትኩረት ከዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት አዝማሚያዎች ጋር የሚጣጣም ሲሆን የኢነርጂ ዘላቂነት አማራጭ ሳይሆን የሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል፡፡
በዐጠቃላይ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የንፁህ የኃይል አቅምን በማስፋፋት፣ ቴክኖሎጂን በማዋሃድ እና መሠረተ ልማትን በማጠናከር ላይ የተመሠረተ ይሆናል፡፡ በኢንዱስትሪ ዕድገት እና በታዳሽ ኃይል መካከል ያለው ትብብር ኢትዮጵያን በአፍሪካ ውስጥ ዘላቂ ኢንቨስትመንት ማዕከል የሚያደርጋት በመሆኑ መንግስት በስትራቴጂካዊ አግባቦች እየመራ ነዉ፡፡ በዚህም የኢንዱስትሪ ስኬቶች፣ በንጹህ ኃይል የሚመሩ፣ ለረጅም ጊዜ ብልጽግና እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት መሠረት እየጣሉ ነው፡፡

