የጣና ሐይቅ ተቀድቶ የማያልቅ የልማት ምንጭ፤ የማይደበዝዝ የውበት ጮራ ነው!

ለባሕር ዳርና ለአካባቢው ዘርፈ ብዙ ትሩፋት ይዞ የመጣውን ፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት ዛሬ መርቀን ለአገልግሎት ከፍተናል።

ዳርቻ የለሽ የተፈጥሮ ውበት ከሰው ልጆች ትጋት ጋር ሲደመር ምን ውጤት እንደሚገኝ ባሕር ዳር ማሳያ ናት።

በባሕር ዳር በኢትዮጵያ ትልቁ ሐይቅ እና በዓለም ትልቁ ወንዝ የሚገናኙባት ከተማ ናት። ዙሪያዋ ፈጣሪ የሰውን መንፈስ በነፍስም በሥጋም ለማደስ የፈጠረው አካባቢ ነው። በወዲያ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት አለ። ተሻግሮ የጎንደር ፋሲለደስ ደረቱን ነፍቶ ይታያል። መነሻ በወዲህ በገበታ ለሀገር ኢኒሼቲቭ ተጠንስሶ በአቶ ካሣሁን(ቢአይካ) የተገነባው የፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት ይገኛል። በመሐል ዓባይና ጣና ናቸው።

ዛሬ የመረቅነው የፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት ለከተማዋና ለሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተጨማሪ የውበት እና የልማት ከፍታ ነው። መንግሥት ለቱሪዝም መዳረሻዎች የሰጠው ትኩረት ምን ውጤት እንዳመጣ በገሐድ የሚነበብበት ፕሮጀክት ነው። የአካባቢውን የቱሪዝም መሥመርና ሠንሠለት የሚያጠናክር ማረፊያና መዳረሻም ነው።

ሪዞርቱ ዘመናዊ እና ቅንጡ የእንግዳ ማረፊያዎች፣ የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ ሱቆች ፣ አምፊ ቴአትር እና መሰል መሠረተ ልማቶችን አሟልቶ፣ ጣናን ተንተርሶ የተሠራ ሪዞርት ነው።

በባሕር ዳር ኢንቨስት ለማድረግ ሥራ የጀመሩና መሬት የተረከቡ ኢንቨስተሮች እንደ ፈለገ ግዮን ሥራዎቻቸውን በፍጥነት እንዲፈጽሙ አደራ እንላለን።

Similar Posts