የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት
“ዛሬ በኤልዶሬት፣ ኬንያ በተከበረው የማሹጃ ቀን (የጀግኖች ቀን) ብሔራዊ ክብረ በዓል ላይ በመገኘትና ንግግር በማድረግ፤ ለሀገራቸው ነጻነት ለታገሉና ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር ታላቅ መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች ያለኝን ታላቅ ክብር ገልጫለሁ። ለጀግንነታቸውና ትተውት ላለፉት ዐሻራ የላቀ ክብር አለኝ!
የኬንያ የጀግንነት እና የመስዋዕትነት ታሪክ፤ ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመከላከል በአንድነት ከቆሙበት ከኢትዮጵያ የአድዋ ታሪክ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል። እነዚህ የጋራ ታሪኮቻችን ነጻነት በስጦታ የተገኘ ሳይሆን በጀግንነት፣ በአንድነት እና በመስዋዕትነት የተረጋገጠ መሆኑን ያስገነዝቡናል።
ታሪካችን የተሳሰረ እንደመሆኑ ሁሉ የወደፊት እጣ ፈንታችንም እንዲሁ የተሳሰረ ሊሆን ይገባል። በመደመር መንፈስ፤ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለህዝቦቻችን ሰፊ እድሎችን እና የጋራ ብልጽግናን ለመፍጠር በንጹህ ሀይል፣ በመንገድ ትስስር፣ በቴሌኮሙኒኬሽን እና በንግድ ዘርፎች ያለንን ነባር ትብብር ይበልጥ ማጠናከር ይኖርብናል።
ዛሬ ክብር ለተቸራቸው ጀግኖች ሁሉ፣ ላቅ ያለ አክብሮቴን አቀርባለሁ። መልካም የማሹጃ (የጀግኖች) ቀን!”










