መንግሥት ለሚሊዮኖች የሥራ እድል ከመፍጠር በዘለለ የሠራተኛውን ደህንነት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና ሰብዓዊ ክብር የሚያረጋግጡ የሕግ ማዕቀፎችን አጠናክሯል።

ሚያዝያ 23 /2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ መንግሥት ላለፉት ስምንት ዓመታት በጽናት የተራመደበት ሁለንተናዊ የለውጥ ጎዳና፣ ከቁጥራዊ እድገት ባለፈ በዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚዳሰሱ ተጨባጭ ለውጦችን እያረጋገጠ ይገኛል ።

በለውጡ ዓመታት በማኅበራዊው ዘርፍ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ኢትዮጵያ በሰው ሀብት ልማት ያላትን እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ ውጤት ቀይረውታል። በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ በሀገር ውስጥ፣ በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እንዲሁም በዘመናዊው የርቀት ሥራ (Remote Work) አማካኝነት ለ 19,872,846 (አሥራ ዘጠኝ ሚሊዮን ስምንት መቶ ሰባ ሁለት ሺህ ስምንት መቶ አርባ ስድስት ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።

ይህ ስኬት መንግሥት የሥራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ የነደፈው “ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ” ፖሊሲ ውጤታማነትንና የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያውን አቅጣጫ ትክክለኛነት በተግባር ያረጋገጠ ነው።

ውጤቱ የተመዘገበው መንግሥት የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማዘመን፣ የልህቀት ማዕከላትን በማስፋፋትና የኢንተርፕርነርሺፕ ተቋማትን በመፍጠር በወሰደው ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።

ከለውጡ ወዲህ መንግስት የኢንዱስትሪ ግንኙነት ትርክትን ከክርክር ወደ ምክክር በማሸጋገር የሠራተኛውን ደህንነት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና ሰብዓዊ ክብር የሚያረጋግጡ የሕግ ማዕቀፎችን አጠናክሯል። የሠራተኛ መብት መከበር ለኢንዱስትሪ ሰላምና ለምርታማነት መሠረት ነው የሚለው መሪ ቃል የመንግሥት የፖሊሲ ቁልፍ አጀንዳ ሆኖ መቀጠሉ፣ ለፈጠራና ለላቀ የጥራት ደረጃ የሚተጋ ሰራተኛ የመፍጠር ወሳኝ ሂደቶች እንዲጠናከሩ አድርጓል ።

በቀጣይም መንግሥት ፖሊሲዎቹንና ስትራቴጂዎቹን ወደ ተግባር የሚለውጠውን የሠራተኛውን አቅም ለመገንባትና የሥራ ዕድል አማራጮችን ለማስፋት ያለውን ቁርጠኝነት ይገልጻል። ዘላቂ ብልፅግና የሚረጋገጠው በፖሊሲ ጥራት ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪ ሰላምና በሠራተኛው ትጋት በመሆኑ፣ መንግሥት የአሠሪና ሠራተኛን ግንኙነት የሚያጠናክሩ፣ ምርታማነትን የሚያሳድጉና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የሪፎርም ሥራዎችን አጠናክሮ ያስቀጥላል።

ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም

ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication

Similar Posts