መንግሥት ዘላቂ አጀንዳዎች ላይ በማተኮር ሀገራዊ ብልፅግናን የሚያፋጥኑ መዋቅራዊ ለውጦችን በስኬት እያከናወነ ይገኛል።

ሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም

የ’ዲጂታል ኢትዮጵያ’ ን መነሻ ያደረገውና ግልጽነትን ያሰፈነው ዘመናዊ የመንግሥት አገልግሎት ሥርዓት፣ በተግባር ፍሬ እያፈራ ያለ ታላቅ ሀገራዊ ሽግግር ነው። በተለይም የቴሌኮም ዘርፍ ሊበራላይዜሽን እርምጃዎች የውድድር መንፈስን በመፍጠር የኢንተርኔትና የዲጂታል ትስስር ተደራሽነትን በከፍተኛ ፍጥነት ማሳደግ ችሏል ።

ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍትህን ለማስፈን ወሳኝ የሆነው የ”ፋይዳ” ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓትም በተሳካ ሁኔታ በመተግበር ላይ ይገኛል። ይህ ሥርዓት በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ፣ የፋይናንስ አካታችነትን ከማረጋገጡም በላይ የመንግሥትን ሀብት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለማከፋፈል እና ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጥታ እንዲደርስ በማድረግ ረገድ የላቀ አስተዋፅዖ የሚያበረክት ዳግማዊ ህዳሴያችን ነው።

የዜጎችን እንግልት ለማስቀረት እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የመንግሥት አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል አማራጭ የማሸጋገሩ ጥረት ሌላው ተጨባጭ ስኬት የተመዘገበበት መስክ ነው። የተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና የፌዴራል ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን በኤሌክትሮኒክስ መንገዶች መስጠት በመጀመራቸው፣ የቢሮክራሲ ውጣ ውረዶች በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንሱ ተደርጓል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመንግሥት ክፍያዎችን በዲጂታል የክፍያ ሥርዓቶች እንዲፈጸሙ መደረጉ የምዝበራና የሙስና ቀዳዳዎችን በመዝጋት፣ የመንግሥትን ገቢ በከፍተኛ መጠን ለማሳደግ እና ሀብትን ለልማት ስራዎች ለማዋል አስቻይ ዐውድ መፍጠር አስችሏል።

ለዚህ የዲጂታል ሽግግር የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዋነኛ ምሰሶ ሲሆን፣ ዘርፉ በተለይም ለወጣቱ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው። በቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች (ስታርትአፖች) ምቹ ምህዳር ከመፍጠር አኳያ የሕግ ማዕቀፎች መሻሻላቸው እና የፋይናንስ አቅርቦት አማራጮች መስፋፋታቸው፣ ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታት የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል እንድትሆን ጠንካራ መሰረት ጥሏል። መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረት ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ትኩረት ስቦ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ አበረታች ውጤቶች እያስመዘገበ ቀጥሏል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች

https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication

Similar Posts