ማንኛዋም ሴት ከህልሟ እንዳትደርስ፤ ያሰበችውን ሰርታ እንዳታሳካ እንቅፋት የሚሆኑባትን ፆታዊ ጥቃቶች ማስቆም የሁላችንም ኃፊነት ሊሆን ይገባል……
ማንኛዋም ሴት ከህልሟ እንዳትደርስ፤ ያሰበችውን ሰርታ እንዳታሳካ እንቅፋት የሚሆኑባትን ፆታዊ ጥቃቶች ማስቆም የሁላችንም ኃፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ ተናገሩ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሰራተኞችና አመራሮች ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር በተመሰረተው ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች መቆያና መልሶ ማቋቋሚያ ማእከል ተገኝተው ድጋፍ በማድረግ በጋራ አክብረዋል። አገልግሎቱ የንፅህና መጠበቂያና የመማሪያ ቁሳቁሶችን እንዲሁም የምግብ ፍጆታ ግብአቶችን ለማእከሉ ድጋፍ አድርጓል።
የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ እንደተናገሩት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሰራተኞች እለቱን በማዕከሉ ለማክበር ሲመጡ ያዘጋጁትን ድጋፍ ለማስረከብ ብቻ ሳይሆን ማዕከላቱን በበጎ ስራ የተሰማሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዲጎበኙ፤ የአቅማቸውንም ድጋፍ እንዲያደርጉ ለማስታወስ ጭምር ነው።
መገናኛ ብዙሃንም ማእከላቱ ያሉበትን ሁኔታ ቀርበው በመመልከት ድጋፍ አድራጊን እና ድጋፍ ፈላጊን ለማገናኘት እንዲችሉ፤ ከአንድ ቀን በአል አከባበር ባሻገር ለጉዳዩ የተሻለ ትኩረት እንዲሰጡ ለማስገንዘብ እንደሆነም ነው የጠቀሱት።
ሴቶች በሕይወት ጉዞ ውስጥ ብዙ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ምንም እንኳን ፈታኝ ጉዞ ቢጠብቀንም ዛሬ ልናደርጋቸው የምንችላቸው በርካታ ተግባራት መኖራቸውን ግን ልንዘነጋ አይገባም ብለዋል፡፡ ለአብነት አንዲት ሴት ጥቃት ደርሶባት የህክምና ድጋፍ ለማግኘት፣የወንጀል ምርመራ ለማድረግ፣ የስነልቦና ድጋፍ እና ጊዜያዊ መጠለያ ለማግኘት የተለያዩ ተቋማት ደጆችን ለመርገጥ እንደምትገደድና ለብዙ እንግልትም እንደምትጋለጥ አንስተዋል። ይህ ደግሞ ተደራራቢ ኢ ፍትሃዊነት ነውም ብለዋል።
ይህንንም ለማስቀረት መንግስት በመላ ሃገሪቱ ለጥቃት የተጋለጡ ሴቶች የሚያስፈልጓቸውን አገልግሎቶች በአንድ የሚያገኙባቸው የአንድ ማዕከላት እየተስፋፉ መሆኑን ሚኒስትር ዲኤታዋ ጠቅሰዋል።
ከዚህ ባሻገር በአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር የተቋቋሙት ሁለት የመጠለያና መልሶ ማቋቋሚያ ማእከላት ውስጥ በአሁኑ ወቅት ከ70 በላይ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችና ህፃናት ይገኛሉ። እስካሁንም ማህበሩ ከ1ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሴቶች መጠለያን በማመቻቸት፣ የህግና የህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ እንዲሁም ራሳቸውን ችለው ገቢ እንዲያገኙ የስራ እድሎችንም በመፍጠር የብዙ ሴቶችን ህይወት የቀየረ በመሆኑ ሊመሰገንና ሊታገዝ እንደሚገባው ሚኒስትር ዲኤታዋ ተናግረዋል።
እነዚህን ማዕከላት ማገዝ ማለት ጥቅሙ ዛሬ በውስጡ ለሚገኙትና ለደረሰባቸው ጥቃት ፍትህን ለሚፈልጉት ሴቶች ብቻ ሳይሆን በየቤቱ ብዙ ጥቃትና ጫናን ተሸክመው “ብናገር ምን ይደርስብኝ ይሆን” በሚል ፍርሃት ለተደበቁ ሴቶችም አቅም የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
መንግስታዊ ተቋማት፤ የሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ በጎ አድራጊዎችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ ለእነዚህ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ፍትህን ለማሰጠት ትልቅ ሚና ላላቸው ማዕከላት ድጋፍ እንዲያደርጉም የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡