በኅዳሴ ግድብ ምረቃ ላይ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት መንግሥታት ተጋብዘዋል፡- መንግሥት

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አተኩረው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የኃይል አቅርቦት እና የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮችን በተመለከተ ለተነሡ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያም በቀጣይ መስከረም ታላቁ የኅዳሴ ግድብ እንደሚመረቅ በመግለጽ በመርሐ ግብሩ ላይ ከግድቡ ተጠቃሚ የኾኑ የታችኞቹ የተፋሰስ አገራት መንግሥታት እንዲታደሙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘዉ ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውን ገንዘብ፣ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚገነባ የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ነው፡፡ ግድቡ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ትልቁ የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ነው፡፡ ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተፈተነ ባለበት እና ታዳሽ ኃይል በስፋት በሚቀነቀንበት ዘመን ኢትዮጵያውን የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክት አድርገዉ እውን ያደረጉት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን በታዳሽ ኃይል የሚስተሳስር ነው፤ የኅዳሴ ግድብ፡፡

ይሁን እንጅ ግብጽ ግድቡ በውኃ አቅርቦቷ ላይ ጉዳት የሚያደርስ በማስመሰል ግድቡ እውን እንዳይኾን በርካታ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች፡፡ እውነታዉ ግን በታችኞቹ ተፋሰስ ላይ ጉዳት ከማድረስ ይልቅ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ መኾኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች እና ጥናቶች ሲገለጽ የቆየ ሀቅ ነው፡፡ ግድቡ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት በጎርፍ እንዳይጠቁ፣ ግድቦቻቸዉ በደለል እንዳይሞሉ፣ ዓመቱን ሙሉ የተመጠነ የውኃ መጠን እንዲያገኙ እና የትነት መጠኑ ከታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ግድቦች ያነሰ መኾኑ የውኃ ብክነትን የሚያስቀር መኾኑ፣ በርካሽ ዋጋ ታዳሽ ኃይል ከኢትዮጵያ እንዲያገኙ ማስቻሉ ከሚያስገኛቸዉ ፋይዳዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በአንጻሩ ኢትዮጵያ የኅዳሴ ግድብን በመገንባት የምታገኘዉ ታዳሽ፣ ኃይል፣ የዓሣ ምርት፣ የቱሪዝም ገቢ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ለማግኘት ግን ኢትዮጵያውን ከፍተኛ ወጭ አድርገዉ ግድቡን ገንብተዋል፤ የተፋሰሱ ደኅንነት እንዲረጋገጥ ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ሠርተዋል፡፡ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት እነዚህን መሰል ጥረቶችን በመደገፍ የጋራ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንጻር እንዲሠሩ መንግሥት በተደጋጋሚ ፍላጎቱን አሳይቷል፡፡ ኢትዮጵያውያን የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጠዉን የግድቡን ግንባታ ለማሰናከል የተደረጉ ተደጋጋሚ ጥረቶችን በሚያስፈልገዉ ግንባር ኹሉ በመመከት ለስኬት ማብቃት ችለዋል፡፡

በመጪዉ መስከረም ግንባታዉ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ እንደሚመረቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያበሰሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “”ግብጽ፣ ሱዳን እና የተፋሰሱ ሀገራት መስከረም ወር ኅዳሴን ስናስመርቅ የደስታችን ተካፋይ እንድትኾኑ በምክር ቤቱ ስም ግብዣዬን አቀርባለው” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የኅዳሴ ግድብ የታችኞቹን ሀገራት የውኃ ድርሻ እንደማይነካ የቱርካና ሐይቅ ማሳያ መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ኅዳሴ ለሱዳንም ኾነ ለግብጽ በረከት እንጅ ፍጹም ጉዳት እንደማያስከትልም አረጋግጠዋል፡፡ የኢትዮጵያዉያን ፍላጎትም የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትን ጥቅም መጉዳት አለመኾኑን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት ረገድ ከማንኛዉም የአፍሪካ አገር በላቀ እየሠራች እንደምትገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኅዳሴ ከመመረቁ በፊት መረበሽ የሚፈልጉ አሉ፤ ነገር ግን እንመርቀዋለን!” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ማመንጨትን በውኃ ላይ ብቻ እንዳልገደበች ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “የአይሻ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ግንባታም በራስ ዐቅም እየተጠናቀቀ ነው፤ አሉቶ የጂኦተርማል ኃይልም 98% ደርሷል” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ የምሥራቅ አፍሪካ አገራትን በታዳሽ ኃይል የማስተሳሰር ሥራ ላይ ትገኛለች፡፡ ጂቡቲ፣ ሱዳን እና ኬንያ ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ የሚያገኙ ናቸው፡፡ ታንዛኒያ ደግሞ ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይል ማግኘት ጀምራለች፡፡

Similar Posts