“ብዝኃነት ዐቅም፣ ውበት እና ጌጥ ነው፡፡” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
“ብዝኃነት ዐቅም፣ ውበት እና ጌጥ ነው፤ በዚያዉ ልክ ልንጠቀምበት ይገባል” ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ አስገነዘቡ፡፡
“ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ” በሚል መሪ መልእክት የኅብር ቀን በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ተከብሯል፡፡
በመድረኩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት ክቡር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ብዝኃነት የተሰናሰነ ዐቅም መኾኑን በመረዳት የማንነት፣ የሐሳብ፣ የታሪክ፣ የባህል እና የመሳሰሉትን ብዝኃነቶች የሚያስተናግድ ሥርዐት እየዳበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ብዝኃነት የልዩ ልዩ መገለጫዎች ስብጥር ውጤት በመኾኑ የላቀ ዐቅም እና ውበት የሚፈጥር ጌጥ እንደኾነም አስገንዝበዋል፡፡
ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ በሚል ጭብጥ ላይ ያተኮረ የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የፌዴራል ተቋማት ክትትልና ድጋፍ ዴስክ ተወካይ ኃላፊ እንዳለዉ ሙሉዓለም ደግሞ የብዝኃነትን ዐቅም በሰንበሌጥ ወክለዉ አቅርበዋል፡፡ ሰንበሌጥ ብቻዉን ነፋስ፣ ፀሐይ እና ዝናብ እንደማይቋቋም ያስታወሱት አቶ እንዳለዉ “ሰብሰብ ሲል ግን ጥንካሬን በመጋራት ቤትን ያህል መሠረታዊ መጠለያ ይገነባል፤ የቤት ክዳን በመኾን ከዝናብ እና ፀሐይ ይከላከላል፤ ቤቱንም ማራኪ ዕይታ ይሰጠዋል፡፡ ብዝኃነትም እንዲሁ ነው፤ አንድ ሐሳብ፣ አንድ ማንነት፣ አንድ አመለካከት ብቻዉን ውበትም ዐቅምም ያንሰዋል፤ በርካቶች ሲሰናሰኑ ግን ዐቅምም ውበትም ይፈጥራሉ” ብለዋል፡፡
የኅብር ቀንን በፓናል ውይይት ያከበረዉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ለኾኑ ሠራተኞች ማዕድ አጋርቷል፡፡ ለአጠቃላይ ሠራተኞቹም የመልካም ምኞት መግለጫ ካርድ በክቡር ሚኒስትር ድኤታዉ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ አማካኝነት ተበርክቷል፡፡


