ቴክኖሎጂን ለኢትዮጵያ ልማት በማዋል ረገድ ትብብር እና የፈጠራ ስራዎች ወሳኝ ሚና እንዳላቸዉ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ

የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ቴክኖሎጂን ለኢትዮጵያ ሁሉ አቀፍ ልማት በማዋል ረገድ የላቀ ትብብር እና የፈጠራ ስራዎች ወሳኝ ሚና ያላቸዉ መሆኑን ገለጹ፡፡

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ዛሬ ግንቦት 8/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል የተጀመረዉን የምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የቴክኖሎጂ ኤክሲፖ (ኢቴክስ ኤክስፖ 2025) ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋትና ለሀገሪቱ ልማት ላይ ለማዋል በፈጠራ ስራዎች ጠንካራ ትስስር ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡    

ፕሬዝዳንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከግንቦት 8-10/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄደዉን ትልቁ የቴክኖሎጂ ኮንፍረንስን አስመልክቶ ለሚዲያ አካላት በሰጡት ገለጻ፣ መንግስት ትልቅ ትኩረት በመስጠት ከሚሰራባቸዉ አምስቱ የኢኮኖሚ ምሶሶዎች ዉስጥ የዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ አንዱና ዋንኛዉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ፕሬዝዳንት ታዬ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለመደገፍ ጠንካራ መሠረተ ልማት እና ምቹ የቁጥጥር ማዕቀፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ልዩ ልዩ የንግድ ድርጅቶች፣ ፖሊሲ አዉጪዎችና ተመራማሪዎች ይሄንን ኤክስፖ እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በሴክተሮች ውስጥ አዳዲስ ፈጠራዎችን ማሳየት፣ እንዲሁም ስትራቴጂካዊ አጋርነትን እንዲፈጥሩ አሳስበዋል።

ፕሬዝዳንቱ በጋራ ጥረት እድገትና ብልፅግናን ለማስመዝገብ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን በብቃት መጠቀም መጀመረዋን ጠቁመዋል። ይህንን ሀገራዊ ራዕይ ከግቡ ለማድረስ ኤክሲፖዉ እንደ ወሳኝ መድረክ ያገለግለዋል ብለዋል።

Similar Posts