አረንጓዴ ዐሻራ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘዉን ግብ እዉን የሚያደርግ ነዉ

የአረንጓዴ ዐሻራ መረሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘዉን ግብ እዉን የሚያደርግ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽ አገልግሎት ገለጸ፡፡ መረሃ ግብሩ የውሃ ሀብትንና የብዝሃ ህይወት ጥበቃን በማረጋገጥ ረገድም  ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ የቤተ መንግሥት አስተዳደር እና የኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን አመራርና ሠራተኞች፣ የብልፅግና ፓርቲ  ህብረት አባላት በጋራ ትናንት ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም በመልካሳ ቤተመንግሥት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውነዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባሻገር  የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች ተገኝተውበታል ብለዋል፡፡ መርሐ ግብር ከጀመረ ወዲህ እንኳን የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከነበረበት መመናመን ወጥቶ እድገት እያሳየ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የደን ሀብት መመናመን፣ የአፈር መሸርሸርና ድርቅን ለመሳሰሉ አደጋዎች የመጋለጥ ችግሮች ሲያጋጥሙ እንደነበር አንስተዋል። ይህንን ለመቅረፍም በተከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ ስራዎች ችግሮቹን ለመቅረፍ ያስቻሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በመልካሳ ቤተመንግሥት የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ጎን ለጎንም በግቢዉ የአረንጓዴ ዐሻራ ስራን ጨምሮ እተከናወኑ ያሉ ብዙሃ  የኢኮኖሚ ዘርፎችን ማለትም የሰብል ልማት፤ የዶሮ አርባታ፤ የከብት ማድለብና ወተት ምርት፤ እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራዎች ላይ ምልከታ ተደርጓል፡፡

Similar Posts