ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን የምታቀርባቸው በርካታ ተሞክሮዎች አሏት
“የውሃ ዋስትና ለአፍሪካ ብልጽግና፤ የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ መሪ ቃል”
ኢትዮጵያ ከየካቲት 6 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባኤን እና 39ኛውን የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን በደመቀ ሁኔታ እንደምታስተናግድ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ “የ2063 አጀንዳን ለማሳካት ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና የንፅህና አጠባበቅን ማረጋገጥ” በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ የገለጹ ሲሆን፣ ይህም አህጉሪቱ ለዘላቂ ልማት ያላትን ቁርጠኝነትና የረጅም ጊዜ ራዕይ የሚያንፀባርቅ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን የምታጋራቸው በርካታ ተሞክሮዎች እንዳሏት የጠቀሱት አቶ ተስፋሁን፣ በተለይም ባለፉት ሰባት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 50 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋኑን ወደ 23 በመቶ ማሳደግ መቻሉን አብራርተዋል። በተጨማሪም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በታዳሽ የኃይል አማራጮች የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማሟላት ለጎረቤት ሀገራት ጭምር መትረፍ መቻሉን በዝርዝር ገልጸዋል።
በተያያዘም በከተማ ኮሪደር እና በወንዝ ዳርቻ ልማት ከተሞችን ጽዱና ውብ የማድረግ ሥራ በከፍተኛ ንቅናቄ እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ ተስፋሁን አመላክተዋል። ሀገሪቱ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ፕላስቲኮችን በመከልከል ረገድ የወሰደችው እርምጃ ለዘላቂ ልማት ያላትን ጽኑ አቋም እንደሚያሳይ ጠቁመው፣ በቀጣይም የውሃ ሀብቷን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ሁለንተናዊ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኗን አረጋግጠዋል።
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication

