ኢትዮጵያ የዲጂታልማንነትሥርዓት የመገንባት ጉዞን እዉን እያደረገች ነዉ

ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በፊት የተጀመረዉን የዲጂታል ማንነት ሥርዓት የመገንባት ጉዞን እዉን በማድረግ ላይ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተጀመረዉን የአይዲ ፎር አፍሪካ 2025 ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝቶ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት “ፋይዳ” መሰረታዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምሶሶ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 መረሃግብር አንዱ አካል የሆነዉ የፋይዳ መታወቂያ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ደህንነቱ የተጠበቀ እና በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው ዲጂታል መታወቂያን የመኖሪያ አድራሻን፣ እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን ሳይለይ አንድን ግለሰብ ልዩ በሆነ ሥርዓት እንዲታወቅ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
‘ፋይዳ’ ከመታወቂያ ካርድ በላይ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የዜጎችን ማንነት በማረጋገጥ የዜግነት መብቶቻቸውን እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሳለጥ የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ፋይዳ መታወቂያ ዜጎችን ከአገልግሎት አሰጣጥ እና ከመንግስት ጋር በቀላሉ ለማገናኘት ወሳኝ ሚና የሚጫወት መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን ላይ የዜጎችን የዲጂታል አቅምን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ እርምጃ መሆኑን አመልክተዋል።