እንደ ሀገር ለተመዘገቡ የልማትና ዲሞክራሲ ግንባታ ስኬቶች፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሚና ከፍተኛ ነው – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

(ሐምሌ 25/2017 ዓ.ም) በተጠናቀቀዉ በጀት ዓመት እንደ ሀገር የተመዘገቡ በርካታ የልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ ስኬቶች፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አመራርና ሠራተኞች የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2018 ዕቅድን በአዳማ ከተማ እየገመገሙ ነው። የተቋሙ የዘንድሮ አፈጻጸም ከባለፈዉ ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዉጤታማ የኮሙኒኬሽን ሥራዎች የተመዘገቡበት ዓመት መሆኑ በግምገማዉ ታይቷል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) በመድሩኩ ላይ እንደ ገለጹት፣ በተጠናቀቀዉ በጀት ዓመት እንደ ሀገር የተገኙ የልማትና ዲሚክራሲ ግንባታ ሥራዎች አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግበዋል፡፡

በተለይ ዜጋ ተኮር የሆኑ የልማት ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ፣ በውጭ ንግድ ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መረሐ ግብርና ሌሎች የልማት ኢኒሼቲቮች ተግባራዊ መደረጋቸዉ፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ተጨባጭ ለውጦች መታየታቸዉ፣ እንዱሁም በሰው ሀበት ልማትና በሌሎች ዘርፎች የመዘገቡ ስኬቶች ድርብርብ መሆናቸዉን ዶ/ር ለገሠ ገልጸዋል። ከተገኙ ውጤቶች ጀርባ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሚና ከፍተኛ እንደ ነበርም ዶ.ር ለገሠ አስታዉሰዋል፡፡

በቀጣይ ጊዜያትም በሁሉም ዘርፎች የሀገሪቱ የማንሰራራት ዘመን ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ አሠራርና አደረጃጀት ይበልጥ የማጠናከር ሥራ በትኩረት የሚሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራ ይበልጥ ለማሳለጥ አጠቃላይ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቀናጅተው እንዲሠሩ ከማድረግ አንጻር በትኩረት እንደሚሠራም አስገንዝበዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳም፣ ባለፈዉ ዓመት ዘርፉን አቀናጅተው ለመምራትና ዐቅም ከመገንባትና የመንግሥት መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል፡፡

እንደ ሀገር ዘርፉ ከተጣለበት ኃላፊነት አኳያ በቀጣይ በላቀ ደረጃ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው መሥራት ይጠይቃል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ዐጠቃላይ የዘርፉን አሠራሮች ለማዘመን የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተቋሙ ሥራ አመራር ሥራ አስፈጻሚ አቶ እንዳልካቸዉ ፀጋዬም የበጀት ዓመቱን የዕቅድ ክንዉን አቅርበዉ በሠራተኞች ውይይት ተደርጎበታል፡፡

Similar Posts