ከመረጃ ሉዓላዊነት እስከ መዋቅራዊ ሽግግር
ሚያዝያ 15/8/2018 ዓ.ም
የሀገርን የመረጃ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በተተገበረው የሦስት ዓመት የስታትስቲክስ ልማት ፕሮግራም፣ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የ2.6 ሚሊዮን የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ እንዲሁም ከ23 ዓመታት በኋላ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ሀገራዊ የግብርና ቆጠራ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል። ይህ ርምጃ ሀገሪቱ ከውጭ ተቋማት የመረጃ ጥገኝነት ተላቅቃ የራሷን የኢኮኖሚ ትንበያና ፖሊሲ ደህንነቱ በተጠበቀና አስተማማኝ መረጃ ላይ እንድትመሠርት አቅም የፈጠረ ሲሆን፣ ለዘርፍ ትራንስፎርሜሽኑም እንደ ዋነኛ መነሻ ሆኖ አገልግሏል። በዚህም የማምረቻ ኢንዱስትሪው የገበያ ድርሻ ከ25 ወደ 46 በመቶ ከፍ እንዲል፣ የወርቅ ኤክስፖርት እንዲያድግና የ4ጂ (4G) እና 5ጂ (5G) ኔትወርክ ተደራሽነት እንዲሰፋ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
ከዚህ ጎን ለጎን፣ መንግሥት በስፋት እየተገበረ ያለው የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማት የንግድ እንቅስቃሴን በማቀላጠፍ ኢኮኖሚውን በእጅጉ አነቃቅቷል። ከዚህ ቀደም በተግባር ሲታይ ያልነበረው የከተማ ልማት አሁን ላይ ጥራት ያላቸውን መሰረተ-ልማቶችን፣ አረንጓዴ ትራንስፖርትን፣ ፓርኮችንና የእግር ጉዞ ትራኮችን አካትቶ በመገንባቱ የዜጎችን የኑሮ ጥራት አሻሽሏል። ይህም ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር ተዳምሮ ዜጎች ባሉበት ቦታ የተሻለ ኑሮ እንዲኖራቸው የሚያስችል ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ይገኛል። በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ረገድም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 48 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል፣ የውሃ አስተዳደርን በማዘመንና ከአየር ንብረት ጋር የሚስማማ ግብርናን በመተግበር ኢትዮጵያ ተወዳዳሪና የማይበገር ሥነ-ምህዳር እየገነባች ትገኛለች።
በጥቅሉ እንደ ሀገር የኑሮ ውድነቱን ጫና ለመቀነስ የተወሰዱት የፊስካልና የሞኒተሪ ፖሊሲ እርምጃዎች፣ የመንግሥት ወጪን የመቀነስና የበጀት ጉድለትን የማጥበብ ስራዎች፣ ሰፊ የድጎማ ሥርዓት (በነዳጅ፣ በመሠረታዊ የምግብ ሸቀጦችና ማዳበሪያ ላይ) መደረጉ እንዲሁም አሁን ላይ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የደረሰበት ደረጃና በትላልቅ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ረገድ የታየው ቁርጠኝነት የመንግሥትን የመፈጸም አቅም በተግባር ያረጋገጡ ናቸው። ምንም እንኳ ዓለም አቀፋዊና አካባቢያዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ተጽዕኖ ቢኖራቸውም፣ መንግሥት በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበው የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ውጤት፣ የዲጂታል ኢኮኖሚውን መሠረት የማስፋፋት ስራ እና የዲፕሎማሲው መስክ ስኬቶች ኢትዮጵያ ወደ ላቀ የብልጽግና ምዕራፍ እየተሻገረች መሆኑን የሚያሳዩ የማይካዱ እውነታዎች ናቸው።
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication








