ከዕዳ ጥገኝነት ወደ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት

ሚያዝያ 14 /2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከአሳሪውና ከአባካኙ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓት ወጥታ፣ በዕውቀትና በዲሲፕሊን የሚመራ ጠንካራ የኢኮኖሚ መዋቅር መገንባት ችላለች። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሀገራዊ ጸጋዎችን ወደ ላቀ ምርታማነት ለመቀየርና የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የጀመራቸው ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራዎች፣ ዛሬ ላይ ሀገራችንን በዓለም ፈጣን ዕድገት ካላቸው አሥር ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ አድርገዋታል።

አሁን ላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለያዩ ውስብስብ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች ውስጥም ሆኖ ጠንካራ ዕድገት እያስመዘገበ ይገኛል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት እንደ ሀገር የ9.2 በመቶ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገብን ሲሆን፣ በቀጣይ ዓመት ይህ እድገት ባለሁለት አሃዝ በመሆን ወደ 10.2 በመቶ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ስኬት ኢትዮጵያ በዓለም ፈጣን ዕድገት ካላቸው አሥር ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ያደረጋት ሲሆን፣ ዕድገቱ ከቁጥር ባለፈ የኢንዱስትሪ ዘርፍን ድርሻ ከ3.1 ወደ 3.7 በመቶ በማሳደግ ተጨባጭ መዋቅራዊ ሽግግር የታየበት ነው። በተለይም በግብርና (7.9%)፣ በኢንዱስትሪ (13.2%) እና በአገልግሎት (9.3%) ዘርፎች የተመዘገቡት ውጤቶች ለዚህ ስኬት መሠረት ሆነዋል።

የፋይናንስ ሉዓላዊነት እና የዕዳ አስተዳደር ሀገሪቱ ካጋጠማት የዕዳ ወጥመድ ለመውጣት ባደረገችው ጥረት ባለፉት ስምንት ተከታታይ ዓመታት ምንም ዓይነት የውጭ የንግድ ብድር (Commercial Loan) አለመውሰዷ ትልቅ ታሪካዊ ስኬት ነው። በG20 የጋራ ማዕቀፍና ከአበዳሪዎች ጋር በተደረገ የዲፕሎማሲ ድርድር የብድር ክፍያ ሽግሽግ ማድረግ መቻሉ፣ ኢኮኖሚው እንዲረጋጋና ለልማት የሚውል ተጨማሪ የፋይናንስ አቅም እንዲገኝ አስችሏል። በተጨማሪም አዲሱ የኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ ነዋይ ገበያ (Capital Market) ወደ ሥራ ገብቶ በቅድመ ዝግጅት ወቅት ከታቀደው 240 በመቶ ብልጫ ያለው 1.51 ቢሊዮን ብር ማሰባሰቡ የሪፎርሙን ስኬታማነት በተግባር አሳይቷል።

የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ምህዳር በከፍተኛ ሁኔታ እየሳበ መምጣቱን ተከትሎ፣ በቅርቡ በተካሄደው የኢንቨስት ኢትዮጵያ ፎረም ላይ የ13 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ስምምነት መፈረሙ የሀገሪቱን ተመራጭነት ያረጋግጣል። የግሉ ዘርፍ ከዚህ ቀደም ከነበረበት ደካማ ተሳትፎ ወጥቶ ጠንካራ የልማት አጋር እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል በከፍተኛ የዕዳ ሸክም ተዘፍቀው የነበሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በፖሊሲና በአደረጃጀት ተደግፈው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ተደርጓል።

የመሰረተ ልማት ፍትሃዊነት እና ተቋማዊ ሪፎርም የመሰረተ ልማት ስርጭት ቀደም ሲል ከነበረበት ፖለቲካዊ ትርፍን ማዕከል ካደረገ አካሄድ ወጥቶ፣ የአካባቢን የኢኮኖሚ ጸጋ መሰረት ያደረገ እንዲሆን ተደርጓል። ይህም የመንገድ፣ የውሃና የኢነርጂ መሰረተ ልማቶችን በፍትሃዊነት ለማዳረስ እና የህዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ አስችሏል። በተመሳሳይ በፍትህ ሥርዓቱ፣ በምርጫ ቦርድ እና በመገናኛ ብዙሃን ዘርፎች የተከናወኑ ተቋማዊ ግንባታዎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጠናከር አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሲሆን፣ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመቻል የተጀመሩ ጥረቶችም ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች

https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication

Similar Posts