የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ አመለካከት የመቅረጽ እና ብሔራዊ ጥቅሞችን የማስገንዘብ ሚናዉን በላቀ ደረጃ እንዲወጣ መንግሥት አሳሰበ።

“ዓላማ ተኮር ተግባቦት ለሀገር ግንባታ” በሚል መሪ መልእክት የፌዴራል ተቋማት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን የሥራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ውይይት ተካሂዷል፡፡ በአፍሪካ የአመራር ልሕቀት አካዳሚ ዛሬ የተካሄደዉ የውይይት መድረክ ላይ የዘርፉን አጠቃላይ አቅጣጫ ያመላከቱት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ.ር) ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት በተመዘገቡ ኹለንተናዊ ስኬቶች የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ጉልህ ሚና መጫወቱን አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች እየተፈተነች ወደ ለውጥ ምዕራፍ በገባችበት ወቅት ብዝኃነትን የሚያስናግድ የፖለቲካ ምኅዳር እውን እንዲኾን፣ ለዘመናት በተጠራቀመ የዕዳ ጫና ውስጥ የነበረዉ ኢኮኖሚ በስኬት ሪፎርም እንዲደረግ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የነበረዉ የዋጋ ግሽበት እንዲቀንስ፣ ሰው ተኮር ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲስፋፉ እና ጥራታቸዉ እንዲሻሻል፣ የመረጃ እና የሐሳብ ነፃነት እንዲረጋገጥ በተሠሩ ኹሉን አቀፍ የሪፎርም ሥራዎች ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ጉልህ ሚና መጫወቱን ዶ.ር ለገሠ በንግግራቸዉ አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጅ ከዓለማቀፋዊ ነባራዊ ኹኔታዎች መለዋወጥ እና ከተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የለውጥ ሐሳቦች ስር አለመስደድ አንጻር የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ አመለካከት የመቅረጽ፣ ብሔራዊ ጥቅሞችን የማስገንዘብ፣ የመንግሥትን ፖሊሲና ዕቅድ የማስተዋወቅ እና የማስረጽ ሚናዉን በላቀ ደረጃ መወጣት አለበት ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከነበረችበት ዳገት እየወጣች እንደምትገኝ ያመለከቱት ሚኒስትሩ ለውጡን ከማጽናት ወደ ማንሰራራት ለማሸጋገር በኹሉም የሚዲያ አማራጮች ምልዓተ ሕዝቡን በማሳወቅ በመረጃ ላይ ተመሥርቶ እንዲወስን ማነሣሣት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
ለዚህም የዘርፉን ዐቅም በዕውቀት በአመለካከት፣ በክሕሎት እና በሚዲያ ቴክኖሎጂ ማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
“በኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ውስጥ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሚና” በሚል ጭብጥ ላይ ያተኮረ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ ደግሞ “በፍጥነት እየተለዋወጠ በሚገኘዉ የዓለም ሥርዐት ውስጥ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ዘርፉ ግንዛቤ በመፍጠር እና ለፖሊሲ ጥብቅና በመቆም ድርሻዉን መወጣት አለበት” ብለዋል፡፡
በነባሩ እና ዐዲሱ ሚዲያ ያሉ ዕድሎችን ኹሉ በመጠቀም የተቀናጀ፣ የተናበበ እና ትክክለኛ መረጃ በመስጠት የመንግሥት አጀንዳ የበላይነት እንዲይዝ መሥራት እንደሚገባም አቶ ከበደ አመላክተዋል፡፡ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በፈተናዎች ውስጥ ለተመዘገቡ ስኬቶች የሚዲያዉ ሚና ጉልህ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ከበደ በቀጣይም በሂደት ላይ ያለዉ ሀገራዊ ምክክር፣ መጪዉ ምርጫ እና ሌሎችም ብሔራዊ አጀንዳዎች በስኬት እንዲጠናቀቁ ካለፉት ስኬቶችም ክፍተቶችም ትምህርት ወስዶ ራስን ለላቀ ሥራ ማዘጋጀት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉት የፌዴራል ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች አገልግሎቱ መሰል መድረኮችን በመፍጠር ዐቅም ለመገንባት እና የጋራ መረዳት ለመፍጠር የሚያደርገዉን ጥረት አድንቀዋል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት እንደሰጠ ተጨባጭ ማሳያዎች ቢኖሩም አሁንም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉን የአደረጃጀት፣ የዕውቀት፣ የአመለካከት እና የክሕሎት ክፍተቶች ለመሙላት በርካታ ሥራዎች መሥራት እንደሚጠይቅም አመላክተዋል፡፡

