የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተጨባጭ ስኬት ያስመዘገበ መሆኑን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
***************************************
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያ ታላላቂ የታሪክ እጥፋቶችን ያሳየችበት ስኬታማ እንደነበር በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ብዝኃ ዘርፍን መሠረት አድርጎ የተነደፈዉ ፖሊሲ ኢትዮጵያን ወደላቀ ብልጽግና እያሸጋገረ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ዲጂታል ኢኮኖሚዉ በልዩ ትኩረት ከሌሎች ዘርፎች ጋር ተቀናጅተው የኢትዮጵያን ዕድገት እያፋጠኑ እንደሚገኙም ዶ/ር ዐቢይ አስረድተዋል፡፡
የፐብሊክ፣ ፒፕል፣ ፓርትነርሽፕ ለኢትዮጵያ ልማት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑን ያነሡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአረንጓዴ ዐሻራ ብቻ ቢያንስ ከ48 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር ግምት ሊኖረዉ የሚችል ስኬታማ ሥራ በመንግሥት እና ሕዝብ አጋርነት መከናወኑን አመልክተዋል፡፡
በሪፎርሙ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ለማራቅ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን ማሻሻል፣ የዘርፎች ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ዐቅምን ማሳደግ፣ የማስፈጸም ዐቅምን ማሳደግ እና ዘላቂ የፋይናንስ እና ጥራት ያለው ዕድገት ማረጋገጥ ዓላማ ያደረገ እንደነበር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
በውጤቱም ገቢን ለማሻሻል ሪፎርም እና ቴክኖሎጂ ተተግብሮ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል 120 ቢሊዮን ብር የነበረው ከአንድ ትሪሊዮን መሻገሩንም አስታውቀዋል፡፡
ሪፎርሙ ሳይጀምር በዓመቱ ሪፖርት የተደረገዉን ያክል ኤክስፖርት በዚህ ዓመት በ4 ወራት መሳካቱን አንሥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዕዳ ውስጥ መኖሯን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ23 ቢሊዮን ዶላር ያልበለጠ ዕዳ መኖሩን ገልጸው ችግሩ የተወሰደው የንግድ ብድር በመሆኑ ለተራዘመ ብድር እንዲቀየር ጥረት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
ከ4 ቢሊዮን በላይ ዶላር የዕዳ ሽግግሽ መደረጉን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ዕዳ የመክፈል ችግር የለባትም ብለዋል፡፡ ከዩሮ ቦንድ አንጻር ያለው ሐሳብም ኢኮኖሚያችሁ እያደገ ስለሆኑ ወደ ተራዘመ ብድር አንገባም እያሉ ነው፤ ነገር ግን ዕድገታችንን በልኩ እንዲያዩት እየተሠራ ነው፡፡
ባለፉት ሰባት ዓመታትም አንድም ዶላር የንግድ ብድር አለመወሰዱን አስገንዝበዋል፡፡
ከሩፎርሙ በኋላ የኢትዮጵያ ሪዘርብ በ10 እጥፍ በላይ አድጓል፡፡ የውጭ ቀጥታ እንዲሻሻል ሰፋፊ ሥራ መሠራቱን በመግለጽ በርካታ ኢንቨስትመንት ከውጭ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡
ኢዝኦፍ ዱይንግ ቢዝነስ በጥሩ ሁኔታ ለውጥ እያመጣ ነው፤ ለዘመናት ቆሞ የነበረዉ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትም ጥሩ እየሄደ ነው፡፡
ግብርና ባለፈው ዓመት 7.3 በመቶ አድጓል፤ ከአጠቃላይ ምርምትም 2.3 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ በለውጡ ማግስት 1.5 ሚሊዮን ኩንታል የነበረው ሩዝ ባለፈው ዓመት 63 ሚሊዮን ኩንታል መድረሱን በማንሣት ዕድገቱን አሳይተዋል፡፡ ስንዴ በለውጡ ማግስት 47 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ይመረት ነበር፤ ባለፈዉ ዓመት ግን ከ280 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ተመርቷል፡፡ በመንግሥትና በአርሶ አደር አታካች ሥራ ተሠርቶ ነው፡፡
ቡና ከለውጡ ማግስት 4.5 ሚሊዮን ኩንታል ነው፤ 700 ሺህ ዶላር ተገኝቷል፤ ባለፈው ዓመት ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ቡና ተመርቶ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ከኤክስፖርት ባለፈው ዓመት አግኝተናል፡፡ ይህም ግብርና መር ከተባለው ዘመን የላቀ ነው፡፡
ኢንዱስትሪ አምና 13 ከመቶ አድጓል፤ የአጠቃላይ ምርት ድርሻውም 3.5 ከመቶ ነው፡፡ ኢንዱስትሪዉ ከኮንስትራክሽን ባሻገር ማዕድን እና አምራች ኢንዱስትሪዉ ከፍተኛ ዕድገት አሳይተዋል፡፡
በድምሩ የአምና ዕድገት ሻል ያለ ነበር፤ በዚህ ዓመት ወደ ሁለት አኀዝ ይገባል፡፡
ሪፎርሙ የፋይናንስ ዘርፉን ከውድቀት የታደገ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ሳይበደር ኢኮኖሚዉን መምራት የቻለበት ነበር፡፡
በድምሩ የኢትዮጵያ ሪፎርም እኛም አጋር አካላትም ከጠበቁት በላይ የተሳካ ነበር፤ ለሌሎችም ምሳሌ የሚኾን ነው፡፡ አወንታዊ ሪፖርት አለመስማትና አሉታዊ ሪፖርትን መስማት እንዳለም አመላክተዋል፡



