የንግድ ሚዲያዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበርና ለትውልድ የሚሻገሩ የልማት ሥራዎችን አጀንዳ አድርጎ መስራት ይጠበቅባቸዋል – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የንግድ ሚዲያዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበርና ለትውልድ የሚሻገሩ ሀገራዊ የልማት ሥራዎችን አጀንዳ አድርጎ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

መንግስት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከንግድ ሚዲያዎች ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ እንደሚሰራ ገልጿል።

መንግሥትና የንግድ ሚዲያዎች በሀገር ግንባታ ሥራዎች ላይ ይበልጥ ተቀራርበው መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።

በሀገራዊ ለውጥ ጉዞ የተገኙ ስኬቶችን ማሳወቅ፣ የገጠሙ ተግዳሮቶችን ማስገንዘብ ብሎም የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ተወያይቶ መግባባት ላይ መድረስ የውይይቱ ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የመንግሥተ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በወቅቱ በሰጡት ማብራሪያ፥ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት የተገኙ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን አብራርተዋል።

በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በዲፕሎማሲ መስኮች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ መገናኛ ብዙሃንም የተመዘገቡ ስኬቶች ላይ መረጃዎችን ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ በኩል የበኩላቸውን አዎንታዊ ሚና መጫወታቸውን አመልክተዋል።

ሆኖም ከንግድ ሚዲያዎች አኳያ አሁን ባለንበት ዘመን በመደበኛውም ሆነ በዲጂታል ሚዲያው ተመልካች ለማግኘት ሲባል አንድን ጉዳይ የማስጮህ፣ አውድን ያልተረዳ ዘገባን የማሰራጨት፣ በጥናት ላይ ያልተመሰረተ እና የችኮላ አዘጋገብ እንደሚስተዋል አንስተዋል።

በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ደፈር ብሎ ከመዘገብ ይልቅ አጀንዳዎቹን የፓርቲ ወይም የመንግሥት ብቻ አድርጎ የማሰብ፣ ገለል የማድረግ እና በቸልተኝነት የማለፍ አዝማሚያ መኖሩንም ጠቅሰዋል።

ለሁላችንም ያለችን አንዲት ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ብሔራዊ ጥቅምን ጨምሮ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራና በተናበበ መልኩ በአግባቡ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአሁኑ ወቅት የድህረ እውነት ዘመን መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በመገናኛ ብዙሃኑ ዘንድ በጥራትና በጥናት ከመዘገብ ይልቅ በችኮላ በመስራት መረጃን በፍጥነት የማድረስ ፍላጎትና አዝማሚያ እያየለ ማምጣቱን አንስተዋል።

አንዳንድ ሀገራዊ ጉዳዮችን በስክነትና በጥልቀት እንደማይዘግቡ፣ ተመልካችን ከማጣት ፍርሃት መልካም ውጤቶችን ሳይቀር ለመዘገብ ፍላጎትን ያለማሳየት ችግሮች እንደሚስተዋሉም አንስተዋል።

መገናኛ ብዙሃን ትውልድ ገንቢ እና መልካም አመለካከት የሚቀርጹ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የንግድ ሚዲያዎች አመራርና ባለሙያዎች በበኩላቸው፤ ከመረጃ ነጻነት አኳያ ችግር መኖሩን በመጥቀስ አሁንም በመንግሥትና በሚዲያዎቹ በኩል ተቀራርቦ ከመስራት ይልቅ መፈራራት እንደሚስተዋል ጠቅሰዋል።

ለአብነትም መንግሥት መግለጫዎችን ሲሰጥ የግል መገናኛ ብዙሃንን እምብዛም እንደማይጠራ ያነሱት ተሳታፊዎቹ፤ በቀጣይ የተሻለ ምህዳር ከመፍጠር አኳያ መንግሥትና መገናኛ ብዙሃኑ የጋራ ሃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ፤ በመገናኛ ብዙሃን ለሚስተዋሉ ችግሮች ዋነኛው መፍትሔ የአቅም ግንባታ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ባለስልጣኑ የልህቀት ማዕከል ማቋቋም እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ይህም የባለሙያዎችን አቅም በማዳበር በሀገራዊ ጉዳዮች የጋራ አቋም ለመያዝና ተቀራርቦ ለመስራት ያግዛል ነው ያሉት።

በመገናኛ ብዙሃኑ የሚስተዋሉ ስሜት ተኮር የአዘጋገብ ችግሮችን ለማቃለል እንደሚያስችል አመልክተው፤ ሀገራዊ አጀንዳዎችን በጥልቀት የመዘገብ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ባለስልጣኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን በሰጡት ማጠቃለያ፤ መንግሥት ከመረጃ ነጻነት ጋር በተያያዘ ያሉ ክፍተቶችን ለመድፈን ከንግድ ሚዲያዎች ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

መንግስት መረጃ የማግኘት ነጻነት መረጋገጥ እንዳለበት ሙሉ እምነት እንዳለው የገለጹት አቶ ተስፋሁን፤ በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ ስሜት ቀስቃሽ ለማድረግ ሙሉ ምስል በማያሳይ መልኩ ጉዳዮችን ከአውድ ውጭና ከገደብ ባለፈ የመግለፅ ችግሮች በተደጋጋሚ እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል።

ይህም ችግር አንዳንድ የመንግሥት ተቋማት መረጃን ከመስጠት እንዲቆጠቡ እንደሚገፋፋ አብራርተዋል።

ክፍተቱን በዘላቂነት ለመፍታት በመንግሥት በኩል ዝግጁነት መኖሩን አረጋግጠው፤ በመገናኛ ብዙሃኑ በኩልም መረጃዎችን ሙሉ ምስልን በሚያሳይና አውድን በተረዳ መልኩ መዘገብ እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።

አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎች ከአንድ ስርዓት ጋር የሚያያዙ ሳይሆኑ ለትውልዱ የሚሻገሩ በመሆናቸው የንግድ ሚዲያዎች አጀንዳ አድርገው ሊዘግቡባቸው እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

በሀገራዊ ጉዳዮችና በብሔራዊ ጥቅም ላይ ፈተናዎችን ተሻግሮ መስራት እንዲሁም ትብብርን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ነው የገለጹት።

Similar Posts