“ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ ማቅረብና ግንዛቤ መፍጠር ላይ መገናኛ ብዙሃን በስፋት ሊሰሩ እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ተናገሩ።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ከሃገር ውስጥ የሕዝብ እና የግል መገናኛ ብዙሃን አመራሮች ጋር በመሆን የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የእስካሁን ተግባራትን በመጎብኘት ለፕሮግራሙ ስኬት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ በሚከተላቸው ስልቶች ዙሪያም ምክክር አድርገዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እቅድን ለማሳካት እየተተገበሩ ከሚገኙ ትልልቅ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች መካከል “ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያ አንዱ መሆኑን የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ ዘሚካኤል በውይይቱ አንስተዋል።
መገናኛ ብዙሃንም ለዚህ ሃገራዊ ፕሮጀክት መሳካት ያላቸውን ትልቅ ሚና ተረድተው ስለ “ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያ ምንነትና ጠቀሜታ በቂ መረጃ በመስጠት ዜጎች በመብታቸው የሚገባቸውን አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ላይ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራምን ከማቋቋም ጀምሮ አስፈላጊ የሆኑ የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀትና የመመዝገቢያ መሳሪያዎችንም በማሟላት ምዝገባ መጀመር መቻሉን ያነሱት ዳይሬክተሩ እስካሁን ከ4 ሚሊዮን 190 ሺህ በላይ ዜጎች የ”ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በዚህ አመት መጨረሻም የ”ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያ ተገልጋዮችን ቁጥር ወደ 10 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዷል።