የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን እና የኢትዮጵያዊያንን ዉበት የሚያጎላ ነው፡

|

ኢትዮጵያ የብዝኃ ቋንቋ፣ ብዝኃ ባህልና ብዝኃ ማንነት ሃገር ናት፡፡ ብዝኃነት ለኢትዮጵያዊያን ተፈጥሯችን፣ ዉበታችንና የጥንካሬአችን ምንጭ ነው፡፡ ብዝኃ ማንነት ያለበት ሕዝቦች ሀገር መሆናችን ጸጋችን ነው፤ ብዝኃነት የኢትዮጵያ ተጨባጭ እዉነታና ውብትም ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሂደት አንድ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት በርካታ መንገዶች ተሞክሯል፡፡ ነባሩንና ተፈጥሯችን የሆነውን ብዝኃ ማንነትን በአንድ ወጥ ማንነት ለመቀየር ብዙ ተለፍቶበታል፡፡ በፖሊሲና ተቋማዊ አሰራር ጭምር ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን የተደረገው ሙከራ የተፈለገውን ወጥ ማንነት ያላቸውን ሕዝብ ከመፍጠር ይልቅ የተለያዩ ጥያቄዎችንና ቅሬታዎችን ማስነሳቱ አልቀረም፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የማንነት ጥያቄ ከ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ በተደራጀ መልኩ የመታገያ መሳሪያ ሆኖ ሊወጣ ችሏል፡፡ በማንነት ላይ ተመስርተው የተደራጁ ቡድኖችም የብሔራቸውን መብት ለማስከበር በተለያዩ መንገዶች ትግላቸውን ቀጠሉ፡፡

የብሔሮችን የማንነት ጥያቄን ለመመለስ የተጀመረው ትግልም የሀገሪቱን ህልውና ፈተና ላይ ጥሏል፡፡ በመሆኑም በሂደት ሲቀነቀን የነበረውን የማንነት ጥያቄ ማፈን እንደማይቻል ግልፅ እየሆነ በመምጣቱ በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ማስተናገድ እንደ አማራጭ ቀርቧል፡፡

በመሆኑም በ1987 ዓ.ም የፀደቀው የኢ.ፌ.ዴሪ ሕገ-መንግሥት የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ለሚያረጋግጥ፣ በአንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ማዕቀፍ ውስጥ የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና የባሕላዊ መግለጫዎችን አስፈላጊነትን አፅንዖት ሰጥቷል።
ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የራሳቸውን ቋንቋና ባህላቸውን የማሳደግ፣ እንዲሁም ታሪካቸውን የመንከባከብ መብትን ጨምሮ የራሳቸውን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እንዳላቸው በግልጽ ተደንግጓል።

ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ለማስረፅ፣ ብሔር-ብሔረሰቦች በማንነታቸው እንዲኮሩና እንዲቀራረቡ ብሎም በበዝኃነት ውስጥ የተጠናከረ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዲጎላ ለማድረግ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት የፀደቀበት ቀን የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ተብሎ ተሰይሞ ሲከበር ቆይቷል፡፡

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ሀገራዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መልዕክት፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ በአርባ ምንጭ ከተማ ዛሬ ህዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም እየተከበረ ይገኛል።

የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በየዓመቱ በዚህ መልኩ መከበሩ፤ የህዝቦች ትስስርን በማጠናከር እና በማጎልበት ህብረ-ብሄራዊ አንድነትን በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲገነባ ከፍ ያለ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
ክብረ በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህላቸውንና ማንነታቸውን ለማስተዋወቅና ለመተሳሰር ዕድል ይፈጥራል፡፡

በዓሉ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጋራ ለሀገሪቱ የበለፀገ የባህል ቅርስ አስተዋፅዖ በማበርከት አንድነት አስፈላጊ መሆኑን አጉልቶ የሚያሳይም ነዉ፡፡

በተጨማሪም በዓሉ በየዓመቱ መከበር ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ባህል እንዲሆን፣ ለዘመናት ተግባብተዉና ተስማምተው የኖሩ የሕዝቦች የዳበሩ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና ትውፊቶችን ይበልጥ እንዲደምቁ የሚያደርግ እና ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር በእጅጉ ይረዳል፡፡

በዓሉ የአንድነት፣ የሰላም፣ የመቻቻል እንዲሁም የሕብረ-ብሔራዊነት ቀለም መገለጫ ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያውያን የብዝሃ ባህል፣ ታሪክ፣ እሴትና የተፈጥሮ መስህብ መሆናቸውን ለዓለም የሚያስተዋውቁበት መድረክ እንደሆነም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

እንኳን ለ19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አደረሳችሁ!

ሀገራዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት!

Similar Posts