የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዉሮፓ ጉብኝት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ አጋርነት የሚያጠናክር ነዉ

ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ አጋርነት ለማጠናከር ከግንቦት 14-18/2017 ዓ.ም ፈረንሳይና ጣሊያንን ገብኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በፓሪስ ተገናኝተዉ የተወያዩ ሲሆን፣ የኢትጵያና የፈረንሳይ የኢኮኖሚ ትብብር እና አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር መክረዋል፡፡

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በስትራቴጂካዊ ትብብር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊና ድፕሎማሲያዊ አጋርነት ያላቸዉ ሀገራት ሲሆኑ፣ በተለይ የባህል ጥበቃ፣ በመከላከያ፣ በትምህርት፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች በርካታ የልማት ስራዎችን በጋራ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን በተለይም ቡና ወደ ፈረንሳይ ስትልክ ፈረንሳይ በበኩሏ የትራንስፖርት ቁሳቁሶችና የህክምና መገልገያ መሳሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ በዋናነት ትልካለች። በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ሀገራት በመካከላቸው ያለው የኢኮኖሚ ትስስር እየተጠናከረ መጥተዋል፡፡

ሁለቱም መሪዎች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን አጠናክሮ ለማስቀጠል የተስማሙ በመሆኑ በተለይ ጠንካራ፣ አካታች እና የወደፊት ኢኮኖሚያዊ አጋርነት ለማጎልበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም በጣሊያን፣ ሮም ግብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ ከጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኒ ጋር ተገናኝተዉ  ፍሬያማ ውይይት አካሄደዋል።

በዉይይታቸዉም በኢትዮጵያ እና ጣሊያን መካከል የሁለቱን ሀገራት ድፕሎማሲዊ ትስስር በማጠናከር ለአዳዲስ ኢንቬስትመንት እና የኢኮኖሚ ትብብር እድሎችን ለመፍጠር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች የረጅም ዘመን ወዳጅነት ላይ የተመሠረተውን አጋርነት በተለያዩ መስኮች ይበልጥ ለማጠናከር የጋራ ፅኑ አቋማቸዉን ዳግም አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሊዮ አስራ አራተኛ ጋር በቫቲካን ተገናኝተዉ ተወያይተዋል፡፡ በዚህም ለዓለም ሰላም በጋራ ለመስራት፣ እንዲሁም የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋፋት ተስማምተዋል፡፡

Similar Posts