የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ንረትን ለመቀነስ መንግሥት ምን አደረገ ?

“የኑሮ ውድነት የበርካታ ሀገራት ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በአንዳንድ ሀገራት ከ400 ፐርሰንት በላይ የደረሰ የዋጋ ንረት እየተመዘገበ ነው፡፡

ከአፍሪካም 172 ፐርሰንት የደረሰ የዋጋ ንረት ያጋጠመ ሲሆን በጎረቤት ሀገራት እንኳን 72 ፐርሰንት የደረሰ የዋጋ ግሽበት ተመዝግቧል ።

ከለውጡ ወዲህ መንግሥት አለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ቀድሞ በመገምገም ዜጎች ላይ የሚደርሰውን የኑሮ ውድነት ጫናን በዘላቂነት ለመቀነስ በርካታ ኢንሼቲቮችን ቀርጾ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን በዚህም ከፍተኛ ውጤቶች ተገኝተዋል።

በተለይ የሌማት ትሩፋት እና ምርታማነትን ለማሻሻል በተከናወኑ የተቀናጁ ጥረቶች እንደሀገር አመርቂ ስኬቶች ተመዝግበዋል።

በሌማት ቱሩፋት ኢንሼቲቭ የወልና የቤተሰብ ኢኮኖሚ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ እንዲያሳይ ከማድረጉም በላይ የዜጎቻችን የአመጋገብ ስርዓትን በመቀየር የበለፀገ ምግብ አቅርቦት ተጠቃሚነትን በቤተሰብ ደረጃ እንዲሻሻል አድርጓል ።

ኢኒሼቲቩ ኋላቀር የአመራረትና የአሰራር ዘይቤ እንዲቀየሩ እና የተሻሻሉ ዝርያዎች ወደ ልማቱ እንዲገቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እየበረከተ ሲሆን እንደሀገር የምርት አቅርቦት እንዲሻሻል እና የሥራ ዕድል እንዲፈጠር እያደረገ ይገኛል ።

ከሰብል ምርት አንጻር በ2017 የምርት ዘመን በስንዴና ሩዝ ምርት ብቻ 343 ሚሊዮን ኩንታል መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን ውጤቱ መንግሥት አቅርቦትን በመጨመር የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመቀርፍ የሄደበትን ርቀት ያመላክታል ።

መንግሥት ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ የዜጎችን የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ እና የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት የተለያዩ የድጎማ ሥርዓቶችን እየተገበረ ይገኛል ።

በዚህም ለድጎማ ብቻ 440 ቢሊዮን ብር ያወጣ ሲሆን 160 ቢሊዮን ብር ለደሞዝ ጭማሪ፣60 ቢሊዮን ለሴፍትኔት ፣ 84 ቢሊዮን ለማዳበሪያ እና 40 ቢሊዮን ብር ነዳጅ ላይ ተደጉሟል ።

እጅ አጠር የኅብረተሰብ ክፍልን ለመደገፍ በተማሪዎች ምገባ መረሀ-ግብር የቤተሰብ ጫናን በከፍተኛ ደረጃ ማቃለል የተቻለ ሲሆን በማዕድ ማጋራትና በአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታም ሰው ተኮር ተግባራትን መፈጸም ተችሏል ።

እንደመንግሥት የምርት አቅርቦትን ከማሻሻል፣ የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋትና የዋጋ ንረትን ከመቆጣጠር አንጻር የተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤቶችን እያስገኙ ሲሆን ከረዥም ጊዜ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የዋጋ ንረትን ወደ 11.7 ማወረድ ተችሏል ።

Similar Posts