ውሃ ከሀብትነት ባለፈ የልማትና የሰላም መሰረት ነው” — ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ በ39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ውሃ ከአንድ የተፈጥሮ ሀብትነት ባለፈ የአህጉሪቱ የልማት፣ የፈጠራ እና የመረጋጋት መሰረት መሆኑን ገልጸዋል። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ውሃ የከተሞቻችንን ቅርጽ፣ የእርሻ ስራችንን፣ ጤናንና ሰላምን የሚወስን ዋነኛ ተዋናይ ነው። ኢትዮጵያም ኃላፊነት የተሞላበት የውሃ ሀብት አስተዳደር ለልማት መፋጠን ያለውን ወሳኝ ሚና በተግባር እያሳየች መሆኑን አብራርተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቤቶችና ለኢንዱስትሪዎች ኃይል ከመስጠት ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ብርሃን በመላክ የአፍሪካውያን የጋራ ብልጽግና ምንጭ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ወንዞች ለጋራ ጥቅም በጋራ ሲተዳደሩ የሰላም እና የልማት ሞተሮች መሆን እንደሚችሉ ኢትዮጵያ ማሳያ መሆኗንም ጠቁመዋል። ይህም አፍሪካውያን በራሳቸው እውቀትና ጥረት የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚችሉ ትልቅ ማረጋገጫ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመጨረሻም፣ የተመረጡ ፖሊሲዎችና የፈጠራ ስራዎች ኢትዮጵያን በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ለከፍተኛ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት መጋበዛቸውን ዶ/ር ዐቢይ አብራርተዋል። ይህም አገሪቱ ከጥገኝነት ወደ ምርታማነት እንድትሸጋገር ትልቅ ሚና መጫወቱን ጠቅሷል::

ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች

https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication

Similar Posts