የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዉ ለጠንካራ እና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት መሠረት ጥሏል

መጋቢት 8/2018 ዓ.ም

ባለፉት ሰባት የለዉጥ ዓመታት፣ ኢትዮጵያ በነፃ ገበያ ሥርዓት ተወዳዳሪ የሚያደርጋትን ዐቅም በመፍጠር እና ሥር የሰደዱ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ስብራቶችን በመጠግን ረገድ ተጨባጭ ዉጤቶችን አስመዝገባለች፡፡

እንደ ሀገር የገጠሙን ስብራቶች፡-ቀጣይነት ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ አለመመጣጠን፣ ዘላቂና አስተማማኝ የፊስካል ቁመና አለመረጋገጥ፣ ውጤታማ ያልሆነ የሀብት ድልድል፣ ዘላቂ ያለሆነ እድገት እና የሀብት ልዩነቶችን ማስፋፋት የወቅቱ ወሳኝ ተግዳሮቶች እንደነበር የሚታወስ ነዉ፡፡

እነዚህ መዋቅራዊ ችግሮች የኢኮኖሚ እድገቱን ለአደጋ እንዲጋለጥ በማድረጋቸዉ የባለሀብቶችን እምነት እንዲሸረሸር እና መንግሥት አካታች ብልጽግናን የማምጣት ትልሙና ዐቅሙን ሲፈትኑ ቆይተዋል፡፡

በዚህም መንግሥት ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት እና መልሶ ለማዋቀር የታለሙ ተከታታይ የማሻሻያ ፕሮግራሞችን በመንደፍ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል፡፡ ከ2011 በጀት ዓመት አንስቶ የተጀመሩት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዎች በገበያ ውስጥ ያሉትን የተዛቡ አመለካከቶች ለማስተካከል እና የፊስካል ዲሲፕሊን ለማጠናከር የተወሰዱ እርምጃዎች ዉጤት አምጥተዋል፡፡

በዚህም ከ2017 በጀት ዓመት ጀምሮ ወደ ሙሉ ትግበራ እንዲገባ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተጨባጭ ዉጤት ያስገኘ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ በገንዘብ ፖሊሲ፣ በፊስካል አስተዳደር፣ በሀብት ምደባ ሰፊ ማስተካከያዎች እንዲመጡ እና ኢኮኖሚው ከነበረበት ችግር ወጥቶ ወደ ትክክለኛው የዕድገት ሀዲድ እንዲገባ አስችሏል፡፡

ከተግዳሮቶች ባሻገር ያለውን የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ተስፋ በመረዳት ገቢራዊ የተደረገዉ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ፣ እንደሀገር ለጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት እና ለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል መሠረት በመጣል ለዘመናዊ የኢኮኖሚ ሽግግር አዲስ ምዕራፍን ከፍቷል ፡፡

Similar Posts