የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ምሰሶ እየሆነ ነው
መጋቢት 18/2018 ዓ.ም
መንግስት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ የሆነውን የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ በሰጠው ልዩ ትኩረትና ባደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነዉ፡፡
ዘርፉን ይበልጥ ተወዳዳሪ ለማድረግ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎችም ሀገራዊ የምርት አቅምን ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሸጋገር አድርጓል፡፡ መንግስት ስር ነቀል የፖሊሲ ክለሳ በማድረጉ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲያንሰራራ ምቹ መደላድል ፈጥሯል፡፡
የፖሊሲዉ ዋና ግብ ኢትዮጵያን በዘርፉ ቀዳሚ ተጠቃሚና ተወዳዳሪ ማድረግ ሲሆን፣ ለዚህም የግል ባለሀብቱ፣ የመንግስት ተቋማትና የዜጎች ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ገልፀዋል፡፡
በተለይም በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የተጀመረው “ኢትዮጵያ ታምርት” ሀገራዊ ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪው ምቹ መደላደል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በዚህም ሳቢያ በተለያዩ ምክንያቶች ስራ አቁመው የነበሩ 917 ኢንዱስትሪዎች ዳግም ወደ ስራ እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡
የሀገር ውስጥ የምርት አቅም ዕድገትና የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በዘርፉ የተደረገውን ድጋፍ የሀገር ውስጥ ምርቶች በብዛትና በጥራት እንዲያድጉ አስችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 66.3 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሻሻል የታየበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ዘርፉ በአይነቱ ለየት ያለ የቴክኖሎጂ ሽግግር እያደረገ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ የቴክኖሎጂ እድገት የምርት ጥራትን ከማሳደጉ ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ምቹና መስራት የሚችል ሰፊ የሰው ኃይል እንዳላት የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ዘርፉ የዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ግንባር ቀደም እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በየዓመቱ 350 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ መንግስት የዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የጀመረው የድጋፍና የክትትል ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።



