የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ እድሪስ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ ያነሷቸው ዋና ዋና ሀሳቦች!!

✍7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዲሞክራሲ ሥርዓት ባለቤትነትን እና ለሰላም ያለውን ጽኑ ፍላጎት በተግባር ያረጋገጠበት ታሪካዊ ክስተት ነው። የምርጫው የሀገርና የሕዝብ የህልውና መሠረት መሆኑን መንግሥት በጽኑ የሚያምን በመሆኑ ፍትሐዊ፣ ተአማኒና ወቅቱን የጠበቀ እንዲሆን ከመንግሥትና ከሕዝብ ጋር በቅንጅት ሲሠራ ቆይቷል።

✍የሀገሪቱን የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ በውስጥ እና በውጭ ኃይሎች የተቀናጁ የጥፋት ሙከራዎች ተደርገዋል። መሠረተ ልማቶችን በማውደም እና የዜጎችን ዕለታዊ እንቅስቃሴ በመግታት በሕዝብ ደህንነት ላይ ቀጥተኛ ስጋት ለመፍጠር ተሞክሯል።

✍ሥልጣንን በምርጫ ሳይሆን በኃይል ለመቆጣጠር የሚሹ፣ የሕዝብን ድምፅ የመቀበል ታሪክ የሌላቸውና የጥፋት አጀንዳ አስፈጻሚዎች ምርጫውን እንደ ህልውና ስጋት ተመልክተውታል። እነዚህ ኃይሎች የዲሞክራሲ ሂደቱን ለማስቆም ከምርጫው በፊት፣ በምርጫ ወቅት እና ከምርጫው በኋላ ከፍተኛ የትርምስ እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል።

✍መረጃዎችን በማጋነን እና የሐሰት ወሬዎችን በመፈብረክ በኅብረተሰቡ ላይ ስነ-ልቦናዊ ጫና ለመፍጠር ዘመናዊ ቴክኖሎጂና የሚዲያ አውታሮች በስፋት ጥቅም ላይ ውለዋል።

✍የኢትዮጵያ ሕዝብ የጥፋት ኃይሎቹ ያቀረቧቸውን ሦስት ተከታታይ ማደናቀፊያ ጥሪዎችና ማስፈራሪያዎች ወደ ጎን በመተው ውድቅ አድርጓቸዋል፦ የመጀመሪያው፦ “የምርጫ ካርድ አትውሰዱ” የሚለውን ጥሪ ባለመቀበል ካርድ ወስዷል። ሁለተኛው፦ “በፓርቲዎች የድጋፍ ሰልፍ ላይ አትገኙ” የሚለውን ጫና ጥሶ አደባባይ ወጥቷል። ሦስተኛው፦ “ድምፅ አትስጡ” የሚለውን ማስፈራሪያ ውድቅ በማድረግ፣ ታይቶ በማይታወቅ ከፍተኛ ቁጥር ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመጉረፍ የዜግነት መብቱን አስከብሯል።

✍ይህ የሕዝብ የነቃ ተሳትፎና ውሳኔ ኢትዮጵያውያን የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤት መሆናቸውን እና ማንኛውንም የኃይል እና የትርምስ አጀንዳ የሚያከሽፉ መሆናቸውን በተግባር ያረጋገጠ ታላቅ ክስተት ሆኖ የሚመዘገብ ነዉ።

✍ሕዝቡ በምርጫው ላይ በነቂስ ወጥቶ የተሳተፈው ያለ መስዋዕትነት አይደለም፤ ትልቁን ዋጋ የከፈለው ራሱ ሕዝቡ ነው። ሕዝቡ “ፅንፈኝነትና ሥርዓት አልበኝነት አያስፈልገኝም፤ የሕዝብን ፍላጎት የሚያስቀጥል፣ በሕግ ልጠይቀው የምችል ጽኑ መንግሥት ያስፈልገኛል” የሚል መልዕክት አስተላልፏል፡፡

✍ ሰፊ የሽብር እንቅስቃሴዎች በጸጥታ ተቋማት የተቀናጀና ወቅቱን የጠበቀ አጸፋዊ እርምጃ እንዲክሽፉ ተደርገዋል።

✍በደህንነት ምክንያት ምርጫ ያልተጀመረባቸውን ጥቂት ጣቢያዎ 143 ጣቢያዎችን ሰበብ በማድረግ “ምርጫ ተቋረጠ” የሚል የማደናገሪያ ወሬ ተለቆ ነበር። ከ50 ሺህ በላይ በሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ሂደቱ በሰላም የተከናወነ ሲሆን፣ የዓለም ማህበረሰብና የታዛቢ ቡድኖች በተመለከቱት ሁኔታ የጥፋት ኃይሎች ተሸናፊነትና የእውነት አሸናፊነት ተረጋግጧል።

✍ምርጫውን ማደናቀፍ ያቃታቸው ፅንፈኛ ቡድኖች፣ አሁን ደግሞ ሕዝብን ከአውድ ለማውጣት ሌላ የጥፋት ካርድ ለመሳብ እየሞከሩ ይገኛሉ።

✍በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ውስጥ ተማሪዎች በአንድነት የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ እያዩ በነበረበት ወቅት በተፈጸመ የፈንጂ ጥቃት *የአንድ ተማሪ ሕይወት ሲያልፍ፣ 26 ተማሪዎች ቆስለዋል።

✍ኢትዮጵያ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የተለያየ ሃይማኖትና ብሔር ያላቸው ሕዝቦች በአብሮነትና በመደጋገፍ የኖሩባት፣ በሰላም ምሳሌ የምትሆን ሀገር ናት። ይህንን ብዝሃነት እንደ ጥንካሬ በመቁጠር ተደምረን ሀገር የመገንባት ታሪካችን የትናንትም፣ የዛሬም፣ የነገም ሆኖ ይቀጥላል።

✍የ“ሻኔ” የሽብር ቡድን በአርሲ ዞን፣ አሰኮ ወረዳ፣ ደለታ ጨፌ ቀበሌ ላይ ጥቃት ፈጽሟል። በጥቃቱም መጀመሪያ ከፀጥታ አካላት ጋር ግጭት ተፈጥሮ 5 ሚሊሻዎች እና 3 የፖሊስ አባላት ተሰውተዋል።

የጸጥታ አካላቱ ሕዝቡ እንዲሸሽ ጥረት ቢያደርጉም፣ 4 ሲቪሎች ተገድለዋል። በተጨማሪም አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ አንድ የመንግሥት ጤና ጣቢያ እና 65 የግለሰብ ቤቶች ተቃጥለዋል።

✍በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ለቤተክርስቲያን ግንባታ ንዋያትን ለማንቀሳቀስ የተቀረጹ የቆዩ ቪዲዮዎችን በመጠቀም፣ “ቤተክርስቲያን በስደት ላይ ነች” በሚል ሕብረተሰቡን በአሉታዊ መልኩ ለማቀስቀስ የተደረገው የሐሰት መረጃ ስርጭት በሃይማኖትም ሆነ በሞራል ስህተት ነው።

✍መንግሥት እና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የበላይ አመራሮች ጋር በቅርበት በጥልቀት በመወያየት በጥቃቱ መጠን፣ መንስኤና በአጥፊዎቹ ፍላጎት ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል። በቀጣይም የሃይማኖት አባቶች ቦታው ድረስ ሄደው ሁኔታውን እንዲመለከቱና መሰል ችግሮች እንዳይደገሙ አብሮ ይሰራል።

✍ሁኔታው ሃይማኖታዊ መልክ ይዞ ወደ አጠቃላይ ግጭት እንዳያመራ ራሳቸውን የጠበቁ የመንፈሳዊ ወጣቶች ማህበራትና የሃይማኖት አባቶች ላሳዩት ማስተዋል እናመሰግናለን።

✍ነገሮችን በስሜት ሳይሆን እውነታውን መነሻ አድርጎ በልኩ የማየት ባህል ሊኖረንይገባል። ችግሮች ሲከሰቱ ወዲያውኑ ወደ ሚዲያ ከመሮጥ ይልቅ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በመወያየት፣ ለተጎዱት ድጋፍ ማድረግና በቀጣይ መፍትሄ ላይ መምከር ያስፈልጋል።

✍የውስጥና የውጭ ኃይሎች ማኅበራዊ እሴቶችን በመንካት ሕዝቡን ወደ ግጭት ለመክተት የሚያደርጉትን የሚዲያና የስነ-ልቦና ጦርነት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በማስተዋልና አብሮነቱን በማጠናከር ሊያከሽፈው ይገባል።

ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች

https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication

See less

Similar Posts