የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት

“በዚህ ታሪካዊ ሀገራዊ ምክክር የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለመታደም በመታደሌ ታላቅ ኩራት ይሰማኛል።

በሚቀጥሉት ሳምንታት አራት ሺህ ተሳታፊዎችን በአንድ ጣሪያ ስር የሚያሰባስበው ይህ ታላቅ ጉባኤ፣ ኢትዮጵያ በገዛ እጇ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የሚያስችላትን “ብዕርና ብራና” ያገኘችበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።

‎የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ በኃይለ ቃል ጀምሮ በኃይለ እርምጃ የሚደመደምበትን አዙሪት ሰብረን በንግግርና በውይይት የምንተካበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ለዚህ ታላቅ ጉዞ መሳካት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ያለኝን ታላቅ ምስጋና አቀርባለሁ።

‎በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በማሳተፍ ከሥር ወደ ላይ በዘለቀው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ላይ የተመሰረተው ይህ ጉባኤ፣ በቀላሉ የማይደገም እና በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ግዙፍና ታላቅ ዓላማ ያለው ነው:: በዚህም ፈተናዎቻችንን ወደ መልካም አጋጣሚዎች በመቀየር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ባህልን እናጸናለን::

‎በዛሬው ዕለት ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ መልካም ዘሮችን እንዘራለን፤ ከሚያፈራውም ፍሬ ልጆቻችን እንዲጠቀሙ እናደርጋለን:: በዚህ ምክክር ላይ ስንሳተፍ ከየሰፈራችን ወጥተን ለኢትዮጵያ ስንመክር፣ ለልጆቻችን ስንልና እነርሱን እያሰብን ስንወያይ ውጤቱ እጅግ ፍሬያማ ይሆናል። አብረን ተስፋን፣ ይቅርታን እና በጋራ መኖርን እንትከል፤ በሀገር ውስጥ በሚደረግ ውይይትና ይቅርታ ችግሮቻችንን በመፍታት ሀገራችንን ከውጭ ጣልቃ ገብነት እንጠብቅ። ተሳታፊዎች በሙሉ ለኢትዮጵያ መልካም፣ ለአፍሪካ አስተማሪ፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን ደግሞ እውነተኛ እረፍትን የሚያመጣ ታሪካዊ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ጥሪዬን አቀርባለሁ:: “

‎ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!

ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication

Similar Posts