ተቋማት ሲጠናከሩ ሀገር ትጸናለች፤ የዴሞክራሲ ሥርዓትም መሠረት ይይዛል!!

ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም

ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናን፣ ዘላቂ ሰላምን እና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ ባለፉት ዓመታት ያከናወነቻቸው ጥልቅ ተቋማዊ ማሻሻያዎች እና ያስመዘገበቻቸው ተጨባጭ ውጤቶች መሠረት እየያዙና እየጸኑ መጥተዋል።

ሀገር በጠንካራ ተቋማቶቿ ትገልጻለች፤ ለዚህም መንግሥት ለተቋማት መጠናከር በሰጠው ትኩረት ሀገራዊ ሉዓላዊነት በጽናት የሚያስከብሩ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓትን የሚተክሉና የሕዝብን ውሳኔ ሰጪነት የሚያረጋግጡ ለትውልድ ተስፋ፣ ለቀጠናው ደግሞ አስተማማኝ ኩራት የሚሆኑ ተቋማት እየተፈጠሩና ውጤታማ አፈጻጸምም እያሳዩ ይገኛሉ።

በለውጡ ዓመታት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የጸጥታ ተቋማት ከነበሩበት የፖለቲካ ወገንተኝነት ሙሉ በሙሉ ነፃ በመውጣት በዘመናዊ የውትድርና ሳይንስ፣ በሙያዊ ብቃት እና በጽኑ ሀገራዊ ፍቅር ብቻ እንዲመሩ ተደርገዋል። በዚህም ተቋማቱ በላቁ ቴክኖሎጂዎችና በሰለጠነ የሰው ኃይል ተጠናክረው፣ ሕዝባዊ መሠረታቸውን ያሰፉ፣ በሕግ የበላይነት የሚመሩ እና የሀገርን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር የሚችል የማይደፈር አቅም ፈጥረዋል።

የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር በተወሰደው የቁርጠኝነት ርምጃ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ልምምድ አዲስ ተስፋ መሆን ችሏል። ተቋሙ ያደረገው ጠንካራና ውጤታማ የሪፎርም ሥራ በሰባተኛው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ በተግባር እንዲገለጥ አድርጓል።

ተቋሙ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮችን በመመዝገብ፣ ከ47 በላይ ፓርቲዎችን እና ከ10 ሺህ በላይ ዕጩዎችን አወዳድሯል። በሂደቱም ለፖለቲካ ፓርቲዎች ምቹ ዐውድ በመፍጠር፣ የሎጀስቲክስ አቅርቦቶችን በብቃት በመምራት እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፈታኝ ሁኔታዎችን የሚሻገር የሀገር ተስፋ የሆነ ተቋም ኢትዮጵያ እየገነባች ነው የሚል ቀጠናዊ ትርክት መፍጠር ችለናል ።

ልዩነት የጥፋት መሣሪያ ሳይሆን፣ የህብረ-ቀለም ማሳያ የምንደምቅበት ጌጥ ነው። በሀገራችን ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ የሃሳብ ልዩነቶች እና መሰረታዊ አጀንዳዎች ላይ በባለቤትነትና በአካታችነት መንፈስ ለመወያየት የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነጻነቱን ጠብቆ ኢትዮጵያን አሸናፊ አድርጎ ቀጥሏል።

ኮሚሽኑ የህብረተሰቡን ክፍሎች፣ የፖለቲካ ልሂቃን እና ባለድርሻ አካላት ያካተተ ውይይት በማድረግ፣ በሰላማዊ መንገድ ዘላቂ ሀገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ ታሪካዊ ስራዎችን ማከናወን ችሏል። ይህ ተቋም የዜጎችን ድምጽ እኩል በማስተናገድ ረገድ ያሳየው አፈጻጸም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል ከዜሮ-ድምር ፉክክር ወደ መደማመጥ እና መግባባት ለማሸጋገር ትልቅ መሠረት ሆኗል።

ተቋማት ሲጠናከሩ ሀገር ትጸናለች፤ የዴሞክራሲ ሥርዓትም መሠረት ይይዛል። ዛሬ ላይ እያየናቸው ያሉት የመከላከያ እና የጸጥታ ተቋማት ሁለንተናዊ አቅም፣ የምርጫ ቦርድ የሪፎርም ሥራዎች እና የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋማዊ ጥንካሬዎች የኢትዮጵያን ብሩህ ፀሐይ እና የሕዝባችንን የሰላም ዋስትና የሚያረጋግጡ ማሳያዎች ናቸው። እነዚህ ተቋማት ይበልጥ ነጻ፣ ብቁ እና ሕዝባዊ አገልጋይ ሆነው እንዲቀጥሉ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች

https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication

Similar Posts