የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ጉዞ፡ በተግባር የታነጸበት ስራ
“ዛሬ በሞጆ ተገኝተን ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስኬት ትልቅ ሚና የሚጫወተውንና በ60 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባውን ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፍያ የመጀመሪያ ምዕራፍ አስመርቀናል። ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በዓመት እስከ 1 ሚሊዮን ባለ 20 ጫማ ኮንቴነሮች የማስተናገድ አቅም ያላቸው ጣቢያዎችና ዘመናዊ መጋዘኖች ያሉት ሲሆን፣ የደረቅ ብትን ጭነቶችን በሀገር ውስጥ እንድናሽግ ማስቻሉ፣ የውጭ ምንዛሬን ከመቆጠብ ባለፈ ለዜጎቻችን ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። የማዕከሉን የአሰራር ፍጥነት ለማሳደግ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተተከለው የባቡር ላይ ክሬን ከባቡር መስመር የሚደረገውን የኮንቴነር ዝውውር በከፍተኛ ፍጥነት ያከናውናል።
ሙሉ አሰራሩ በዘመናዊ ዲጂታል መሰረተ ልማት የተሳሰረ በመሆኑ፣ ለተገልጋዮች ፈጣን እና አስተማማኝ አገልግሎትን ያሳልጣል። ይህ ማዕከል ከኢትዮ-ጅቡቲ መስመር ባሻገር ኢትዮጵያን፣ ደቡብ ሱዳንን እና ዩጋንዳን የሚያስተሳስረው የ‘ደሱ’ ኮሪደር አካል ሲሆን፤ ይህም ሀገራችን በዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ደረጃ ላይ ያላትን ስፍራ የሚያሻሽልና የቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስራችንን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግር ትልቅ ድል ነው።”













