የወርሀ ነሐሴ እና መስከረም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁልፍ ተግባራት ቅኝት
አረንጓዴ ዐሻራ፦
“ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የቆየው የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር መጠናቀቁን ምክንያት በማድረግ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተካሄደ ሲሆን በመርሃ ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በጋራ ተሳትፈዋል።
ማኅበራዊ ጉዳይ፦
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመትን እና የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። አዲሱን ዓመት በማስመልከትም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች የበዓል ስጦታ ያበረከቱ ሲሆን በጽሕፈት ቤቱ ውስጥ ለሚያድጉ ሕፃናትም የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶችን አበርክተዋል። በተጨማሪም ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር በመሆን ማዕድ አጋርተዋል።
አስተዳደራዊ ጉዳይ፦
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ59ኛው የሚኒስትሮች መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የመሩ ሲሆን ምክር ቤቱ በፌደራል የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ወሰን፣ በብሄራዊ ዳታ አስተዳደር፣ የኃይል ዘርፍ ማሻሻያ፣ የፌደራል ገቢ ግብር ማሻሻያ ደንብ፣ የፌደራል ተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያ ደንብ እንዲሁም የብሄራዊ መከላከያ ሰራዊት ረቂቅ አዋጅ ማሻሻያ ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
ፕሮጀክቶች ማስጀመሪያ እና ምረቃ፦
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአዲስ ዓመት ዋዜማ የሞጆ ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ የመጀመሪያ ምዕራፍን መርቀዋል። ማስፋፊያው በ60 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባ ሲሆን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የምታደርገውን ጉዞ በተግባር ያረጋገጠችበት ነው። በውስጡም በዓመት እስከ 1 ሚሊዮን ባለ 20 ጫማ ኮንቴነሮችን የማስተናገድ አቅም ያላቸው ጣቢያዎችና ዘመናዊ መጋዘኖች ይገኛሉ።
ዲፕሎማሲ እና የሁለትዮሽ ግንኙነቶች፦
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና በዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) መካከል ታሪካዊ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈርሟል። ስምምነቱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ልዩ የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችል ሲሆን ይህ አጋርነት 1.5 ሚሊዮን ቤቶች የዜጎችን ክብር በሚጠብቅ መልኩ ተገንብተው በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ የሚያስችልና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያረጋግጥ ወሳኝ እርምጃ ነው።
በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕንድ አዘጋጅነት በተካሄደው 18ኛው የብሪክስ መሪዎች ጉባዔ ላይ ተሳትፈዋል። ከጉባዔው ጎን ለጎንም ከሕንድ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፣ ኢራን፣ ማሌዢያ፣ ካዛኪስታን እና ቬትናም መሪዎች ጋር በሁለትዮሽ ትብብር መስኮች ዙሪያ መክረዋል። ጉባዔውም ኢትዮጵያ ወደ ኮፕ32 እያደረገች ያለችውን የእመርታ ጉዞና ዝግጅት የደገፈ ሲሆን የዓለም አቀፉን የንግድ ድርጅት የመቀላቀል ሂደት ያበረታ እንዲሁም በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የአፍሪካ ተወካይ ዕጩነት በሙሉ ድምጽ የተቀበለ ፍሬያማ ጉባዔ ነበር።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወር በጅቡቲ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በቆይታቸውም ከፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦመር ጊሌ እና ከአሊኮ ዳንጎቴ ጋር በመሆን የአፍሪካውያንን ትብብር የሚያረጋግጠውን የደወሌ–ዳርመጆግ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክትን መርቀው አስጀምረዋል። መሠረተ ልማቱ ከጅቡቲዋ ዳርመጆግ እስከ ኢትዮጵያዋ ደወሌ ድረስ 120 ኪሎ ሜትር ያህል የሚዘልቅ ሲሆን ይህም በጅቡቲ ዳርመጆግ የሚገኙትን የባሕር ላይ ነዳጅ መቀበያና የባሕር ዳርቻ ማከማቻ ተቋማት በኢትዮጵያ ደወሌ ከሚገኙት የሀገር ውስጥ ማከማቻና ማስፋፊያ ተቋማት ጋር ያገናኛል፤ በዚህም የተቀናጀ የነዳጅ ሎጂስቲክስ ሥርዓት ይዘረጋል።
በወሩ መጨረሻም የሶማሊያውን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼኽ መሐሙድን በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተቀበሏቸው ሲሆን በተጨማሪም በኬንያ በተካሄደው የላሙ ነዳጅ ማጣሪያ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተሳትፈዋል።
#PMOEthiopia













