ኢትዮጵያ በአስመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን እንዲዘጋ ወሰነች

|

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአስመራ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለመዝጋት መወሰኑን አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ ከኤርትራ በኩል ለተሰነዘሩ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ላልሆኑ ጠብ ጫሪ እና የጠላትነት ድርጊቶች የአጸፋ ምላሽ በመስጠት፣ በኤርትራ አስመራ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲውን ለመዝጋት ውሳኔ ማስተላለፉን ገልጿል።

ሚኒስቴሩ አያይዞም የቪዬና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ስምምነት ድንጋጌዎችን በመጣስ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት ላይ ቀጥተኛ አደጋ በሚፈጥሩ ሕገ-ወጥ ተግባራት ውስጥ ተሳትፈዋል ያለቻቸውን 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶች ከሀገር እንዲሰናበቱ መታወጁን አመልክቷል።

እነዚህ ዲፕሎማቶችም በ48 ሰዓታት ውስጥ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ መታዘዛቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የኤርትራ መንግሥት ከሉዓላዊ ሀገራት የግንኙነት መርሆች ጋር ፈጽሞ የሚቃረኑ ማናቸውንም ድርጊቶች እንዲያቆም አሳስባለች።

ሀገሪቱ ከኤርትራ ጋር ያላትን ጠንካራ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ዋጋ እንደምትሰጥ የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ሀገሪቷ በሰላም አብሮ መኖርን፣ ለቀጣናዊ መረጋጋት እና ለትብብር ሁልጊዜም ቅድሚያ እንደምትሰጥ አመልክቷል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ፍላጎቷን በመግለጽ፤በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘላቂ ሰላም፣ደህንነትና ቀጣናዊ ትስስር እንዲሰፍን ከቀጣናው አገራት በሙሉ ጋር በቅርበት ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኖኗን ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውቋል።

ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication

Similar Posts