የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት
“ኢሬቻ ሰላም ነው! ገዳ ስልጣኔ ነው! የኢትዮጵያ ስልጣኔ አይቀሬ ነው!
እንኳን የክረምቱን አስቸጋሪ ወቅት በሰላም አሳልፋችሁ ለብሩሁ ብራ አደረሳችሁ። የክረምቱ ጨለማ አልፎ የብራዋ ጀንበር ስትወጣ ኦሮሞ በአንድነት ወጥቶ በባህሉ ስርዓት ወደ መልካ ይሄድና የክረምቱን ጨለማ ያሳለፈውን ፈጣሪውን ያመሰግናል። ለሚመጣውም ጊዜ ተስፋን ይሰንቃል። አባቶች “ማሬሆ” እናቶች ደግሞ “አራሮ” በማለት ለቸሩ አምላክ ምስጋና ያቀርባሉ። ወደ መልካው በመውረድም የምስጋና ስርዓቱን ያስጀምራሉ።
የክረምቱ ጨለማ በርካታ የማይመቹ ነገሮች አሉት። የሰውንና የእንስሳትን እንቅስቃሴ በመገደብ ያሰቡበት እንዳይደርሱ ያደርጋል። የክረምቱ ዶፍ ዝናብ፣ ጎርፉ፣ ጭቃውና አንሸራታቹ ድጥ ብራን በእጅጉ ተናፋቂ ያደርጋል። ለዘመናት የቆየው አብዛኛው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት፣ የፖለቲካ ባህርይና አስተዳደርን ከክረምቱ አስቸጋሪ ወቅት ጋር ማመሳሰል እንችላለን።
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ሆና ሳለች የስሟን ያክል መሆን ሳትችል ቆይታለች። በርካታ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶች እያሏት በዕውቀትና በስርዓት ስላልተመራ ብቻ ወደ ተጨባጭ አቅም መቀየር ባለመቻሏ የድህነት ተምሳሌነት ሆና ስትጠቀስ ኖራለች። የረጅም ዘመናት ሀገረ መንግስትነት ቢኖራትም የህዝብን ችግር የሚፈታና ሀገርን የሚያሻግር ዘመናዊ አስተዳደር ለመገንባት ግን ስትቸገር ቆይታለች። ከራሷ አልፎ አለም አቀፍ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችል መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ቢኖራትም አልተጠቀመችበትም። ከዚህ የተነሳ በእህል ጎተራ ላይ ተቀምጣ የምትራብ፣ ውሃ እያላት የምትጠማና እያለዉ ያጣ ህዝብ ሆነን ኖረናል።
የክረምቱ ጨለማ ማለፉ የተፈጥሮ ህግ ነው። የክረምቱ ዝናብ ሲያልፍ በጎ ነገርም ትቶ ይሄዳል። የዝናቡ ውሃ መሬት ውስጥ ዘልቆ አፈሩን አርሶ አዝርዕት ያበቅላል፤ የተዘራውን ዘር አብቅሎ እንዲያፈራ ያደርጋል፤ የብራውን አበባ አፍክቶ ተስፋን ያለመልማል። የብራው አበባ መዓዛው ያውዳል፤ ቀለሙም ይማርካል፤ የተዘራው ሰብልም በብራ ወቅት ፍሬው ይሞላል፤ ለዚህ ነው ኦሮሞ ለብራ ትልቅ ስፍራ ያለው።
ህዝባችን በትግሉ ያመጣው ለውጥም ከብራ ጋር ይመሳሰላል። ለኢትዮጵያ የሰነቅነው የብራ ራዕይ፡ ጠንካራ አንድነት ላይ የተመሠረተች ፣ ሉዓላዊነቷ የተከበረ፣ በስፋት የምታመርትና ማንኛውንም ዓይነት ፈተና የምትቋቋም ለአፍሪካ ግንባር ቀደም ተምሳሌት የሆነ ሀገር መገንባት ነው። ኢትዮጵያን ወደ ስልጣኔ የማሻገር ስትራቴጂያዊ እቅድ በተግባር ላይ እየዋለ ነው። በእቅዱ መሠረትም የለውጡ መንግስት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ወደ ዕድል እየቀየረ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካው መስክ ታላላቅ ውጤቶችን እያስመዘገበ ነው። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ፣ ሀገራዊ ምክክር በተሳካ ሁኔታ መከናወኑ፣ እንደ ማዳበሪያ ፋብሪካና የነዳጅ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የቢሾፍቱ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መጀመራቸው የስልጣኔ ጀንበር ለኢትዮጵያ ብቅ እያለች ለመሆኗ ጥቂት ማሳያዎች ናቸው።
የኦሮሞ ህዝብ ቋንቋውን፣ ባህሉንና እሴቱን ለማሳደግ ያነሣውን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ለመመለስ በባህል ልማት ረገድ የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ ወደ መልካው ተመልሶ ስርዓት ውስጥ መግባቱ፤ የሆራ ሀርሰዴ ኢሬቻ ደግሞ በቢሾፍቱ ውብት ደምቆ ከፍ ብሎ መከበሩ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።
አሁን የምንገነባው ስልጣኔ በጥንታዊ እሴቶቻችን ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በመደመር ፍልስፍና አቅደን ለጋራ እውቀት፣ የገዳና የሰፉ ትምህርት፣ ለጋራ ፍትህ ባህላዊ ሸንጎዎችን አቋቁመን፣ ለጋራ ልማት የዜግነት አገልግሎትን ዘርግተን፣ ለጋራ ደህንነት ደግሞ የስርዓቱን ጠባቂዎች አደራጅተን ስርዓት እየገነባን እንገኛለን።
ለኢትዮጵያ መውጣት የጀመረው ይህ የለውጥ ብርሃን በየትኛውም የክረምት ጨለማ፣ ዶፍና ጭቃ ተንሸራትቶ ሊደናቀፍ አይችልም። ፈተናዎች ግን አሁንም ይኖራሉ። እነዚህ ፈተናዎች ግን ከኢትዮጵያና ህዝቦቿ አቅም በታች ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን አንድነቱን አጠናክሮ፣ ወንድማማችነትን አስፋፍቶ በፍቅር በመደመር የኢትዮጵያን ስልጣኔ እውን ለማድረግ እየተባበረ ይገኛል። እኛም በህዝብ ድምፅ እንደተመረጠ መንግስት ከእሴታችን በፈለቀው የመደመር እሳቤ ላይ ተመስርተን የኢትዮጵያን ስልጣኔ ዕውን ለማድረግ ተግተን በመስራት ላይ እንገኛለን። የአድዋ አባቶቻችንን ጀግንነት በማስቀጠል ኢትዮጵያን ከጠላት እየጠበቅን ነን። እነርሱ ባሰመሩልን ድንበር ውስጥ እኩልነት፣ ሰላምና ብልፅግና እንዲረጋገጥ በፅናት እየሠራን እንገኛለን። የገዳ ስርዓት እሴትን መነሻ በማድረግ የሀሳብ ልዩነትን በመደማመጥ ለማስተካከል ሀገራዊ ውይይት አድርገናል።
በሌላ በኩል ደግሞ “እኔ ስጋ ብቻ ልብላ፤ እንስሳዬ ግን እንዳይነካ” የሚል ጠላትና ባንዳ ፊት ቆመን የሀገራችንን ጥቅም እናስከብራለን። መንገድ ስተው ከሀገራቸው በተቃራኒ ለቆሙ ወንድሞቻችን ያለን መልእክት ኦሮሞ ‘ከሚያመሹበት የሚያድሩበት ቤት ይሻላል’ ብሎ እንደሚተርት አሁንም ፊታቸውን ወደ ሰላም ከመለሱ፤ የሰላም በር እንደተከፈተ ያለ መሆኑን ላረጋግጥላቸው እወዳለሁ። ኦሮሞ በትግሉ ነፃ ወጥቷል። ከዚህ በኋላ በጠብመንጃ አፈሙዝና ከጠላት ጋራ በመወገን የሚመለስ የኦሮሞ ጥያቄ ፈፅሞ አይኖርም።
የተከበርከው ህዝባችን ሆይ፣
የኢሬቻን በዓል ስናከብር እንደ እሴቱ አንድነትን አጥብቀን፣ እጃችንን ለሰላምና ለዕርቅ ዘርግተን፣ ቀልባችንን ወደ ይቅርታ መልሰን ስላገኘነው ነገር ፈጣሪን እያመሰገንንና እየተንከባከብን ያጣነውን ደግሞ በትዕግስት በመጠበቅ፤ ልክ ትናንት ኦሮሞ በአባቶቹ ደምና አጥንት ኢትዮጵያን እንደገነባ፣ ዛሬም የኢትዮጵያን ስልጣኔ ዕውን ለማድረግ ባለን ዕውቀት፣ አቅምና ሀብት ሁሉ ከሌሎች ወንድም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን በግንባር ቀደምነት ኢትዮጵያን እንድናፀና ጥሪዬን አቀርባለሁ!”
ኢሬቻ ሰላም ነው! ገዳ ስልጣኔ ነው! የኢትዮጵያ ስልጣኔ አይቀሬ ነው!
ከለቻና ጫጩው የሰላም ይሁን!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!
መስከረም፣ 2019 ዓ.ም.
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication





