መስከረም 18 ቀን 2019 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 59ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የአስፈጻሚ አካላትን አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግስት እና ምርጫ ህግ በየአምስት አመቱ የሚደረገውን ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 56 መሰረት አዲስ የአስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ማደራጀት የሚጠበቅ በመሆኑ፣ በ2018 ዓ.ም በተደረገው ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎ የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን በአዲስ መልክ ለማቋቋም እንዲያስችል ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
2. ቀጥሎም ምክር ቤቱ የተወያየው ብሔራዊ የዳታ አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ግቦችን ለማሳካት፣ የዳታ ደህንነትንና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፣ የዳታ መጋራትን፣ የዳታ ተናባቢነትንና የዳታ መልሶ አጠቃቀምን በማጠናከር የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማዘመን፣ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ምርምርና የፈጠራ አቅምን ለማጎልበት፣ የኢኖቬሽንና የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን እና በዳታ የተመራ የኢኮኖሚ ልማት ሥርዓት ለመገንባት እንዲያስችል ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቁ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
3. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር በተፈረመው ለኃይል ሴክተር ሪፎርም፣ ኢንቨስትመንትና ዝመና ምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የአንድ መቶ አርባ አምስት ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺ ኤስ.ዲ.አር ብድር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ምክር ቤቱም ስምምነቱ ከሀገራችን የብድር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣም መሆኑን በማጋገጥ ረቂቅ አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
4. የፌዴራል ገቢ ግብር ማሻሻያ ደንብ ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት አጀንዳ ነው፡፡ ደንቡ የፌዴራል የገቢ ግብር ግልጽነትንና አስተዳደራዊ ቅልጥፍናን ለማረጋገጥ እና ከተሻሻለው የፌዴራል ገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማድረግ እንዲቻል የተሻሻለውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/2009 እንደገና ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
5. እንዲሁም ምክር ቤቱ የፌዴራል ተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያ ደንብ ላይ ተወያይቷል፡፡ ቀደም ሲል የሙያ አገልግሎት እና ሌሎች አቅርቦቶችን እየሰጡ የተርን ኦቨር ታክስ ይሰበስቡ የነበሩ ግብር ከፋዮች የተርን ኦቨር ታክስ የተሻረ በመሆኑ እነዚህ ግብር ከፋዮች ለተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝግበው ታክሱን እንዲሰበስቡ ለማድረግ፣ በአንዳንድ አቅርቦቶች ላይ የተጣለው ታክስ ለህብረተሰቡ በሚቀርቡ መሰረታዊ አቅርቦቶች እና በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነት ላይ ጫናን ያሳደረ በመሆኑ አቅርቦቶቹን ከታክሱ ነፃ ለማድረግ እንዲያስችል ማሻሻያ ደንቡ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
6. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ተቋሙ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 87 ድንጋጌዎች መሰረት የተሰጡትን ሃገራዊ ተልዕኮዎች በህግ አግባብ ለመፈፀም እንዲችል የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ቁጥር 1286/2015 ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡




