ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የራስን ሀብት በራስ ዐቅም ማሳካት እንደሚቻል የሚያሳይ ዐዲስ የፓንአፍሪካኒዝም አብነት ነው፡- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ታላቁ የኢትዮጵያ ግድብ ከኃይል ማመንጫ ግድብነት ባሻገር በራስ ዐቅም የራስን መሻት ማሳካት እንደሚቻል ያሳየ ዐዲስ የፓን አፍሪካኒዝም አብነት መኾኑን የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ተናገሩ፡፡
ሚኒስትር ዲኤታዉ አርቲ አፍሪካ ባዘጋጀዉ የአፍሪካ የሚዲያ ዕውቅና መድረክ ዋዜማ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም ማእከልነቷን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በራስ ዐቅም በማሳካት እንደገና ማስቀጠሏን አመልክተዋል፡፡
“ኢትዮጵያውያን ላብ፣ ደም፣ ገንዘብ እና ዕውቀት አዋጥተው በሉዓላዊ ግዛታቸው ውስጥ የራሳቸዉን ውኃ ለመጠቀም ግድቡን እውን ያደረጉት በቀደምቶቹ ፓንአፍሪካዊ ዕሳቤ ተመርተው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለላቀ ፓን አፍሪካዊ ድል የሚያነሣሣ ሌላ ዐዲስ መሠረት ነው” ብለዋል አቶ ተስፋሁን በመልእክታቸው፡፡
የነበሩ ትርክቶችን የለወጠ፣ የዓለምን ትኩረት የሳበ እና የኢትዮጵያን የመቻል ዐቅም ያሳየ ፕሮጀክት እንደኾነ ያስታወሱት ሚኒስትር ዲኤታዉ “ሕዳሴ የግጭት ሳይኾን የአንድነትና የትብብር ማእከል አስኳል፣ የውኃ አጠቃቀም ፍትሐዊነት ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡
የሩሲያዉ አርቲ የሚዲያ ተቋም ባዘጋጀዉ የአፍሪካ ሚዲያ ዕውቅና መድረክ ለመታደም የመጡ የሃገራት ኮሚኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ሚንስቴሮችና ተወካዮች፣ የቀድሞ ፓን አፍሪካኒስት መሪዎች ልጆች፣ የአፍሪካ አገራት የሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎች እና በአህጉሩ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ትናንት ምሽት በነበረው የእንግዶች የመክፈቻ ንግግር ላይ መልእክት ያስተላለፉት አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ “የበለጸገች፣ የተባበረችና የተረጋጋች አፍሪካን ያልሙ የነበሩ ቀደምቶቻችንን መሻት ለማሳካት ልጆቻቸዉ እና የሚዲያ ተቋማት ኢትዮጵያ ላይ በመገኘታችሁ ደስ ብሎናል፤ ኮርተናልም፡፡ አሁንም በቀደምቶቻችን የአንድነትና የትብብር መንፈስ የአህጉራችንን ጸጋ እናለማለን፤ የበለጸገች አፍሪካን እውን እናደርጋለን፤ የተዛቡ ትርክቶችንም እንገራለን” ብለዋል፡፡
ለዚህም ከህዳሴ ግድምብ ባሻገር በአካባቢ ጥበቃ (አረንጓዴ አሻራ) ሥራዎች፣ የከተሞችን ልማት ጽዱና ምቹ በማድረግ፣ በኤአይ እና ሌሎችም የኢኮኖሚ መስኮች ከፍተኛ እመርታ እያስመዘገበች መሆኑንና ይህንን ለመታዘብና ለመዘገብ ከአርባ በላይ የሕዝብና የንግድ ሚዲያ ሃላፊዎች መምጣታቸው ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል። ለዚህም ውድድሩን በማዘጋጀት ከፍተኛ ሚና ለተወጣው አርቲ ሚዲያ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በምሽቱ መርሐ ግብር ላይ የኔልሰን ማንዴላ፣ ኩዋሜ ንኩርማህ፣ ፓትሪስ ሉሙምባ፣ ጁሊዬስ ኔሬሬ፣ ኬኔት ካውንዳ እና ሌሎችም የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ የቀድሞ መሪዎች ልጆች፣ የሚዲያ ኃላፊዎች እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተገኝተዋል፡፡የአፍሪካ ሚዲያ ዕውቅና መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ይካሄዳል፡



