“ኅብራችን ለሰላማችን”

ኅብረ ብዙ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለኅብር ቀን በሰላም አደረሳችሁ!
ጳጕሜን 4 የኅብር ቀን “ኅብራችን ለሰላማችን” በሚል መሪ መልዕክት ተከብሮ ይውላል፡፡ በእርግጥም የኅብር ቀን ኢትዮጵያውያን ዓመቱን ሙሉ ልናከብረዉ የሚገባ ነው፤ ኅብራችን ብዙ ነውና፡፡ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በአመለካከት፣ በመልክዓ ምድር፣ በአመጋገብ፣ በአኗኗር ዘይቤ፣ በአለባበስ ወ.ዘ.ተ፡፡ ኅብራዊነታችን ሰፊ ነው፡፡ ይህ ኅብራችን ደግሞ ውበታችን፣ ሀብታችን፣ የደስታና የጥንካሬያችን ምንጭ ነው፡፡ የደገኛዉ አለባበስ ለቆለኛዉ ብርቁ ነው፤ የአንዱ ብሔር አጨፋፈር ለሌላዉ ዐዲስ ልምድና የደስታ ምንጩ ነው፡፡ የአንዳችን አመለካከት ለሌላችን ትምህርት ነው፡፡ በአንድ አካባቢ ያለዉ መልክዓ ምድር ለሌላኛው ጌጥ ነው፡፡
ኅብር ተፈጥሯዊ በሆነባት ኢትዮጵያ የብዝኃነትን ትሩፋት እየተካፈሉ መኖር መታደል ነው፡፡ ይሁን እንጅ በአንዳንዶች ኅብርን በልኩ አለመገንዘብ ላይ የታሪካዊ ጠላቶቻችን ሴራ ታክሎበት ልዩነቶችን ወደ ዋልታረገጥነት በመጎተት ሰላማችን ሲፈትን ቆይቷል፡፡ ኅብራዊነታችን ውስጥ ስንጥቅ ፍለጋ የሚኳትኑ ተላላኪዎችና ታሪካዊ ጠላቶች ሲያቆራቁሱን ኖረዋል፡፡ ለዘመናት በዘለቁት ልምዶቻችንም በቂ ትምህርት ወስደናል፡፡ ብዝኃነትን የሚኖር የሰከነ ባህልና ትውፊት ያለው ሕዝብ አለን፤ ብዝኃነታችንን በሚገባ የሚያስተናግድ ኅብረ ብሔራዊ ሥርዐት በጥልቅ መሠረት ላይ ተገንብቷል፡፡ ፈተናዎቻችን ለመሻገር እየተመካከርን ነው፤ የአመለካከት ልዩነቶቻችን ለማጥበብና ለማስማማት አጀንዳ አድርገን እየመከርን ነው፡፡
የኅብር ቀንን “ኅብራችን ለሰላማችን” በሚል መሪ መልእክት የምናከብረዉም ብዝኃነታችንን በሁለንተናዊ መልኩ ለመገንዘብ፣ በብዝኃነታችን ውስጥ ያሉ ጸጋዎችን ለማስተዋወቅና ለመጠቀም፣ እየገነባናት ያለችው ኢትዮጵያ ብዝኃነቷ በብዙ መልኩ የነበረ፣ ያለና የሚኖር መሆኑን በመገንዘብ የማክበር ልምድን ለማዳበር ነው፡፡ በመጪዉ ዐዲስ ዓመትም ኅብራችንን ለሰላም እሴት ግንባታችን፣ ኅብራችንን ለልማት ዕቅዶቻችን ስኬት፣ ኅብራችንን ለሁለንተናዊ ብልጽግችን እንጠቀምበታለን፤ አንዳችን ከሌላኛችን ብዙ እናተርፍበታለን፡፡
መልካም የኅብር ቀን!
