ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ እና በቀይ ባሕር ዙሪያ ያላትን መልክዓ ምድራዊ እና ታሪካዊ እውነታዎች በማንኛውም ኃይል ሊቀየሩ አይችሉም – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ መነሻ ስትሆን፣ ከሞላ ጎደል አብዛኛው የዓባይ ውሃ የሚመነጨው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ነው፡፡
ወንዙ ለናይል ወንዝ አጠቃላይ የውኃ መጠን 85 በመቶውን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም እና አስተዳደር ዙሪያ የሚደረጉ ማናቸውም ውይይቶች እነዚህን መሠረታዊ እውነታዎች ያገናዘቡ መሆን አለባቸው ብሏል፡፡
በተመሳሳይ ቀይ ባሕር ኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ እና ታሪካዊ ትስስር ያላት የውኃ አካል መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፤ በጊዜ ሂደት የፖለቲካ ድንበሮች ቢቀያየሩም ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት የጠበቀ ቁርኝት ዛሬም እንደቀጠለ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡
የኢትዮጵያ ቅርብ የተባለው ድንበር ከባሕር ዳርቻው 48 ኪ.ሜ ብቻ ርቀት ላይ እንደሚገኝም አብራርቷል፡፡
በመሆኑም በቀጣናዊ የባሕር ላይ ጉዳዮች እና የደኅንነት መዋቅር ላይ የሚደረግ ማንኛውም ውይይት የኢትዮጵያን ሕጋዊ ጥቅሞች እና ከቀይ ባሕር ጋር ያላትን ዘላቂ ትስስር ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት ሲል አሳስቧል፡፡
እነዚህ መልክዓ ምድራዊ እና ታሪካዊ እውነታዎች በፖለቲካዊ ዲስኩር፣ በማስገደድ እርምጃዎች ወይም ሀገርን በማተራመስ ድርጊቶች ሊቀየሩ እንደማይችሉ የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ በተላላኪዎች አማካይነት የሚወሰዱ እርምጃዎች ወይም የጥቃት ድርጊቶች መሬት ላይ ያለውን እውነታ እንደማይቀይሩት ሁሉ፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ሕጋዊ ጥቅም፣ ሚና እና ኃላፊነት ሊያሳንሱት አይችሉም ሲል አስምሮበታል፡፡
ኢትዮጵያ ሰላማዊ ግንኙነትን፣ የጋራ መከባበርን እና ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር እንደምትቀጥል ያረጋገጠው ሚኒስቴሩ፤ ሉዓላዊነቷን፣ የግዛት አንድነቷን እና ዋነኛ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለመጠበቅ ምንጊዜም ዝግጁ መሆኗን አስታውቋል፡፡
በመጨረሻም ሁሉም የቀጣናው ተዋናዮች የጋራ ፈተናዎችን ከግጭት እና አንዱ ተጠቃሚ ሌላው ተጎጂ ከሚሆንበት (ዜሮ-ድምር) አካሄድ ይልቅ፣ ገንቢ በሆነ ውይይት፣ በአጋርነት እና በመልካም ጉርብትና መርሆች ላይ ተመሥርተው እንዲፈቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል፡፡
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication


