ዛሬ 800 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያውያን ታሪክ ይሠራሉ- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ
እንኳን አደረሳችሁ። ኑ ተስፋን እንትከል!
ዛሬ፣ ታሪካዊ በሆነችው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር፣ ኢትዮጵያውያን 800 ሚሊዮን አረንጓዴ ችግኞችን ይዘው ወደ መሬት ዝቅ ብለው መሬትን ይዳስሳሉ። መሬትም ቃሏን የምታጸናበትና የተቀበለችውን መልሳ በዕጥፍ መስጠት እንደምትችል የምታሳይበት ልዩ ቀን ነው።
ዛሬ 800 ሚሊዮን ችግኞችን ኢትዮጵያውያን በአንድነት፣ በሐሳብና በተግባር አንድነት ወደ መሬት ያወርዳሉ። በዘንድሮው ክረምት 8 ቢሊዮን ችግኞችን እንተክላለን ብለን ዕቅድ ይዘናል። የምንተክለው በሐሳብና በተግባር አንድነት ወደ መሬት የምንወርድበት ትልቁ ምክንያት የነጠፈች፣ የደረቀች፣ የተጎዳች ምድር ስላለችን ነው። ይህን ለማከም በተግባርና በሐሳብ አንድነት የምንሄድበት ትልቁ መነሻ ደግሞ የመደመር መንግሥት ሐሳብ ነው። ኑ፣ በአንድነት የተጎሳቆለችውንና የነጠፈችውን ምድራችንን እናክማት። ዛሬ 800 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያውያን ታሪክ ይሠራሉ።
ውድ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ነዋሪዎች፣ ታላላቅ አዛውንቶች፣ ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣ ወይዛዝርቶች፤ ዛሬ፣ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም. ታሪክ የምንሠራበት ቀን ነው። ከየቀዬው የወጣችሁ ሁሉ በጸና አቅም፣ በበረታ ክንድ፣ በሐሳብ አንድነት፣ በተግባር አንድነት 800 ሚሊዮን ችግኞችን ተክለን ታሪክ ለዓለም ሕዝብ እናስመስክራለን።
ይህ ታሪካዊ ቀን በተግባር ተጀምሯል። ትውልዱ ከየቀበሌው አረንጓዴ ችግኝ ይዞ መውጣት ችሏል። በየሰዓቱ ከዚህ ከመረጃ ማዕከላችን፣ ከኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ ታሪካዊ ሥራችን የደረሰበትን ደረጃ መረጃ እየተለዋወጥን፣ በሐሳብና በተግባር አንድነት የምንዘምትበት ታሪካዊ ቀን ነው።
ኑ ተስፋን እንትከል!
እናት ዓለም መለሰ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication


