የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽንን ጎብኝቼ ነበር። ይህ ተቋም ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው።
ኢትዮጵያ እጅግ ከፍተኛ በሆነ እምቅ አቅሟ እና በተትረፈረፈ ተፈጥሯዊ ሀብቷ ለረጅም ጊዜ ትታወቃለች። አዲሱ ምዕራፍ ደግሞ እነዚህን ሀብቶች ወደ ተጨባጭ ልማት፣ የቴክኖሎጂ እድገት እና ወደ ጋራ ብልጽግና መለወጥ ላይ ያተኩራል።
አስተማማኝና ዘላቂ የኃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪ፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለዲጂታል መሠረተ ልማትና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ማዕከላዊ ሚና አለው። የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ደግሞ የኃይል ዋስትናን በማጠናከር እየገሰገሰ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ፤ ከኃይል ምርት ባለፈ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ለሀገራዊ ልማትና ለቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ መሠረታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ለብሔራዊ የኒውክሊየር ኃይል ፕሮግራም አስፈላጊ የሆኑትን ተቋማዊ እና ቴክኒካዊ መሠረቶች በመጣል ይህንን ርዕይ ለማሳካት ስትራቴጂካዊ ሚና አለው። ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት፣ ሳይንሳዊ ምርምርን ማስፋፋት እና የተቋሙን ዕውቀት ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ወሳኝ ተግባራት ናቸው። ይህም ብሔራዊ አቅምንና ልዩ ሙያዊ ብቃትን በማዳበር የኒውክሊየር ኃይል ልማት ሰላማዊ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂ በሆነ መንገድ በኃላፊነት ስሜት እንዲከወን ያደርጋል።











