የኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ አስደናቂ የሆነ የለውጥ ጉዞ አሳይቷል።
ይህ ጉዞ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር ከግብርና ጥገኝነት ወደ ኢንዱስትሪ በማዞር፣ የውጭ ምንዛሬን በማዳን እና የሥራ ዕድልን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ዘርፉ ከሰነቃቸው ዐበይት ዓላማዎች አንዱ፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የንግድ ሚዛኑን ማስተካከል ሲሆን ይህ ጥረት ባለፉት አራት ዓመታት አስደሳች ውጤቶችን አስገኝቷል፦
የውጭ ምንዛሬ ገቢ፦
የአምራች ኢንዱስትሪው የወጪ ንግድ በ2014 ከነበረበት 358 ሚሊዮን ዶላር፣ በ2018 በዘጠኝ ወራት ብቻ ወደ 433.8 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል። ይህ ማለት በየዓመቱ ከ5 በመቶ በላይ የሚሆን አማካይ አመታዊ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል።
የተኪ ምርት ስትራቴጂ፦
መንግሥት 96 ስትራቴጂክ ምርቶችን በመለየት በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ በማድረጉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል። በዚህም ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት የዳነ የውጭ ምንዛሬ ዕድገት በ2014 በጀት ዓመት ከነበረው 0.343 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2018 ዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ 4.85 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።
የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ የገበያ ድርሻ፦
በተመሳሳይ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በገበያው ላይ ያላቸው ድርሻ በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፤ በ2014 ከነበረው የ30 በመቶ ድርሻ አሁን ላይ ወደ 46 በመቶ ማደግ ችሏል።
ኢንቨስትመንት እና የኢንዱስትሪ መስፋፋት፦
ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በተደረጉ የህግ ማሻሻያዎች እና የመሠረተ ልማት የማስፋፋት ስራ፣ ዘርፉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶችን ቀልብ መሳብ ችሏል። በተለይም ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) አባል በመሆኗ እንዲሁም በሌሎች የዲፕሎማሲ ስኬቶች እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፤ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ አድርገዋል።
በኢንቨስትመንቱ ስራ፤ ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ ከ2,800 በላይ አዳዲስ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶች ማሳካት የተቻለ ሲሆን በአማካይ በየዓመቱ ከ700 በላይ ኢንቨስትመንቶች በመሳብ ከፍተኛ ስኬት መመዝገብ ተችሏል።
የሥራ ዕድል እና ኢንዱስትሪዎች፦
ከ18,000 በላይ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ተዘግተው የነበሩ 993 ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲመለሱ መደረጉ ለኢኮኖሚው እድገት ከፍተኛ አቅም ፈጥሯል።
በአጠቃላይ፣ ይህ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ በገበያ መር የተመሠረተ ዕድገትን እየተቀዳጀ መሆኑንና ቀጣይ መዳረሻው የተሻለ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት መንገድ ላይ መሆኑን በግልጽ ያሳያል።
#PMOEthiopia #EthiopiaDelivers #MadeInEthiopia
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication

