የኮሙኒኬሽን ተቋማት በወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተናበበና የተቀናጀ የመረጃ ተደራሽነትን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸው ተገለፀ

በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተናበበና የተቀናጀ መረጃ ከተቋማት ጋር የመለዋወጥ ዐቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መሻሻል እያመጣ እና ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንና ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ አስታውቀዋል።
የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የፌዴራል እና የተጠሪ ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ የጋራ መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።
ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ማለት በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል የግንኙነት ድልድይ የሚገነባ፣ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃን ተደራሽ የሚያደርግ በመሆኑ በየጊዜው እየተገናኙ ሥራን በመገምገም ዐቅሙን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አቶ ከበደ ተናግዋል፡፡ አገልግሎቱ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና ከተጠሪ ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ጋር በየጊዜዉ ወቅታዊ የመረጃ ልውውጦችን በማድረግ የተቀናጀ እና የተናበበ መረጃ ተደራሽ የማድረግ ሥራዉ እየጎለበቱ መምጣታቸውንም ገልጸዋል፡፡
አገልግሎቱ ለዘርፉ አስፈላጊዉን ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ፣ ሥራዎችን በጋራ በመገምገም ግብዓቶችን በመጨመር እና ገንቢ ግብረ መልስ በመስጠት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ከዚህ በላይ እንዲጠናከር እየተሠራ እንደሚገኝም በንግግራቸዉ አመላክተዋል።
በቀጣይም ተቋማት የተናበበ፣ የተቀናጀ እና ዓላማ መር የኮሙኒኬሽን ሥርዐት በመፍጠር እና ወቅቱን የጠበቀ መረጃን ተደራሽ በማድረግ ሀገራዊ ሕልሞችን ለማሳካት እና ተፅኖ ለመፍጠር ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ አሳስበዋል።
“የተናበበ እና የተቀናጀ የተግባቦት ሥርዐት ለእመታዊ ዕድገት” በሚል መሪ ሐሳብ በተዘጋጀው መድረክ ሀገራዊ የሩብ ዓመት የኮሙኒኬሽን ዘርፍ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ የጋራ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።