የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት

“ኢትዮጵያ ለታሪካዊውና ታላቁ የሀገራዊ ምክክር በምትሰናዳበት በዚህ ወሳኝ ታሪካዊ ወቅት፤ ለመላው የሀገሬ ልጆች የማስተላልፈው ታላቅና የከበረ ጥሪ አለኝ። ነገ የሚጀመረው ውይይት ፍቱን የፖለቲካ መድረክ ብቻ ሳይሆን፣ የእኛን እና የመጪውን ትውልድ እጣ ፈንታና የወደፊት ተስፋ ሙሉ በሙሉ የሚወስን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጭምር ነው።

‎ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋትና ሁለንተናዊ ብልጽግና የምትተጉ፣ የኢትዮጵያ ታላቅነት ግድ የሚላችሁ ሁሉ፤ ፈረሱም ሜዳውም ይኸው!

‎ትናንት አባቶቻችንና እናቶቻችን በዓድዋ ለሀገር ነጻነት፣ ለሉዓላዊነትና ለክብር ሲሉ በደማቸውና በአጥንታቸው እንደተዋደቁላት ሁሉ፣ ዛሬም ኢትዮጵያ የታሪክ አደራ የሚሸከሙ የቁርጥ ቀን ልጆቿን ትፈልጋለች።

ሆኖም ዛሬ ሀገራችን የምትሻው ጠመንጃ ያነገቡ ሳይሆን በሀሳብ ብስለት፣ በእውነት፣ በዕውቀትና በጽናት ታጥቀው የተሰናዱ የሰላም ታጋዮችን ነው። እኛ ዛሬም እንደ ትናንቱ በታላቅ የድል ዋዜማ ላይ እንገኛለን፤ ምክንያቱም የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ ማሸነፍ አይቀሬ ነው!

‎በሰለጠነ ንግግር፣ በሰላማዊ ውይይትና ሀገራዊ መግባባት የገጠሙንን ፈተናዎች በሙሉ አልፈን ወደ ብልጽግና በጋራ እንሻገራለን!”

Similar Posts