ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን፣ ከበርካታ የሀገር መሪዎች ጋር ሀገራዊና አህጉራዊ ፋይዳ ያላቸውን ውይይቶች አከናውነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ዳንኤል ቻፖ ጋር በከተማ ልማት፣ በግብርና እንዲሁም በሰላምና ጸጥታ ዙሪያ ለመተባበር የመከሩ ሲሆን፣ ከታንዛኒያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ጋር ደግሞ በቅድሚያ ትኩረት በሚሹ ዘርፎች ላይ ያላቸውን ግንኙነት ለማሳደግ ተስማምተዋል።
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎው ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሺኬዲ ጋር በነበራቸው ቆይታም በአቪዬሽን ዘርፍ ያለውን ስኬታማ አጋርነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ መክረዋል።
ከሶማሊያ እና ሴኔጋል መሪዎች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ የመከሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከላይቤሪያው ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ቦአካይ ጋር ደግሞ ኢትዮጵያ አህጉራዊ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዩኒቨርሲቲ ለመገንባት ባላት እቅድ እና በቴክኖሎጂ ትብብር ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
በተጨማሪም ከሊቢያው ፕሬዝዳንታዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ መሐመድ አል-መንፊ ጋር በቀጣናዊ ልማት ዙሪያ፣ እንዲሁም ከቦትስዋናው ፕሬዝዳንት ዱማ ቦኮ ጋር በኢኮኖሚ ትብብርና ተተኪ የአፍሪካ መሪዎችን በማፍራት ዙሪያ ተወያይተዋል።
እነዚህ የሁለትዮሽ ውይይቶች ከአፍሪካ ሀገራት ባለፈ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋርም የተደረጉ ሲሆን፣ ይህም የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ይበልጥ እያጠናከረው መጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይም ይህንኑ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ አጠናክረው እንደሚቀጥሉና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication








