ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላተ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ማብራሪያ ክፍል -1
ሀገራዊ ሪፎርምና ጠንካራ የኢኮኖሚ ስርዓት ግንባታን በተመለከተ
በዓለም ላይ እየተፈጠረ ባለው የንግድ ስርዓት መዛባት፤ እንዲሁም በዋና ዋና ምርቶች ላይ ባጋጠመው የምርት እጥረትና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪና የእድገት መገራገጭ አጋጥሟል። ነገር ግን በኢትዮጵያ ሲከናወን በቆየው የኢኮኖሚ ሪፎርም ስራ ምክንያት ፈተናዎችን የሚቋቋም አቻዮ የኢኮኖሚ ስርዓት መገንባት ችለናል።
የኢኮኖሚ መልሶ ክለሳን በተመለከተ
ባለፉት አስራ አንድ ዓመታት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ክለሳ ተካሄዶ አያውቅም። በመሆኑም አዳዲስ የተጨመሩ ኢኮኖሚዎችን ለማካተትና ሚና የሌላቸውን የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለማስወጣት ባለፉት አንድ ዓመታት ከፍተኛ የሰው ኃይል በማሰማራት የኢኮኖሚ ክለሳ ሲካሄድ ቆይቷል። ከዚህ በፊት በኢኮኖሚ ያልተካተቱ ዲጂታል ኢኮኖሚ፣ የኮሪደር ልማት፣ ክላስተር ግብርና፣ ሌማት ትሩፋት፣ ተጨማሪ ኢንዱስሪ ፓርክ ፣ አረንጓዴ አሻራ፣ አዳዲስ የኢነርጂ ፕሮጀክቶች ። ኮንፈረንስ ቱሪዝም፣ የቱሪዝም መሰረተ ልማት፣ ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎችን የሚለካ ስርዓት አልነበረም። ክለሳውም እነዚህንና ሌሎችን በማካተት ተሰርቷል።
የባቡር መሰረተ ልማትን በተመለከተ
የኢትዮ- ጅቡቲ ባቡር ኮርፖሬሽንን ለማሻሻል በተከናወኑ ስራዎች ከዚህ በፊት ይገኝ የነበረውን ትርፍ ከ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወደ 43 ቢሊዮን ብር ማሳደግ ተችሏል። የነበሩትን ሎኮሞቲቮችን ከ11 ወደ 36 ማሳደግ የተቻለ ሲሆን፤ አሁን ላይ ከአንድ ሺህ በላይ ጋሪዎችንም ማስተዳደር ችሏል። የመንገደኞችን አገልግሎትም ከ198 ሺህ ወደ 588 ሺህ አሳድጓል። ከጋርጎ አንጻርም ወደ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን ካርጎ ማሳደግ ተችሏል። ከ95 በመቶ ያላነሰ የቡና ኤክስፖርት እንዲሁም 25 በመቶ የማዳበሪያ ገቢ ንግድም በባቡር እየተከናወነ ነው። አሁን ላይ ወደ 100 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ስራዎችን በራስ አቅም እየገነባን ነው። ይህ ትልቅ ስራ ነው።
የኢትዮጵያን ጥቅል ዓመታዊ ምርት በሚመለከት
በኢኮኖሚ ክለሳው መሰረት የኢትዮጵያ ጥቅል ዓመታዊ ምርት 210 ቢሊዮን ዶላር በመሆን ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት 3ኛው ትልቁ ኢኮኖሚ መሆን ችሏል። ይህ ሂደት በጥብቅ ዲሲፕሊን የተመራ ነው።
ኢንዱስትሪ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከግብርና የተሻለ ድርሻ መያዝ ችሏል!
ግብርና ከጥቅል ዓመታዊ እድገታችን 31 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ አለው። ኢንዱስትሪ ደግሞ 31 ነጥብ 8 በመቶ ድርሻ በመያዝ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቅል ዓመታዊ እድገታችን ከግብርና የተሻለ ድርሻ መያዝ ችሏል። ይህ እንግዲህ ኢንዱስትሪው በፍጥነት እያደገ መሆኑን የሚያመላክት ነው።
የግብር መሰረት ማስፋትን በተመለከተ
ኢትዮጵያ ውስጥ የግብር መሰረትን የማስፋት ስራን በደንብ ማየት ይገባል። በርግጥ ግብር መክፈል ክብር ነው። ሁሉም ዜጋ ይህን በደንብ መገንዘብ አለበት ። ታማኝ ግብር ከፋዮች አሁንም በጣም ጥቂት ናቸው። ከጥቅል ዓመታዊ ምርታችንም አንጻር የሚሰበሰበው ግብር በጣም ትንሽ ነው። ስለዚህ ይህን በአሰራርና በህግ ማስተካከል ይገባል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስን በተመለከተ
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረበት 2 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ሃብት ዛሬ 9 ትሪሊዮን ደርሷል። ትልቅ ይወድም የነበረ ሃብተን በማሰባሰብ አጠቃላይ ሃብቱን በሶስት እጥፍ ማሳደግ ችሏል። ከገቢ አንጻርም አሁን ላይ 3 ነጥብ 1 ትሪሊዮን ብር ያስገባል። ባለፉት 3 ወራት ብቻ 72 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል። ይህም የመንግስት ሃብት ከመበዝበዝ ወጥቶ ትርፍ ሃብት እንዲያስመዘገብ የተሰራው የሪፎርም ስራ ውጤት ተመዝግቦበታል።
የዲጂታል ፋይናንስን በተመለከተ
በኢትዮጵያ የባንኮች ተቀማጭ 5 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር ደርሷል። አጠቃላይ የማባይል ባንኪንግ ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥርም 70 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን በኢትዮጵያ 11 ትሪሊን ብር በዲጂታል ፋይናንስ ይዘዋወራል። ይህም በተለይ የብድር አቅርቦትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ አቅም ፈጥሯል።
የወጪ ንግድን በተመለከተ
ከወጪ ንግድ አንጻር ባለፉት ሶስት ወራት 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ከወጪ ንግድ ማግኘት ተችሏል። ይህ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ እድገት አለው። ከሀገራዊ ሪፎርሙ በፊት ካሉ ዓመታት ጋር ካነጻጻርነው ደግሞ የአንድ ዓመት የወጪ ንግድ ገቢ ጋር የሚስተካከል ነው። ይህ ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም እያላት በአሰራር ውስንነት ተይዛ እንደነበር የሚያሳይ ነው።
ነዳጅን በሚመለከት
ወደብ ሳይኖረን፣ የነዳጅ ዴፖ ሳይኖረን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያጋጠመውን የነዳጅ ቀውስ ለመቋቋም በከፍተኛ ድጎማና ነዳጅ ቁጠባ ያከናወነው ስራ ምስጋና የሚቸረው ነው። በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ነዳጅ በድጎማ ማምጣት ብቻ ሳይሆን ያስተዳደርንበት መንገድ ከፍተኛ ምስጋና የሚቸረው ተግባር ነው።
ነዳጅ ዋጋን በተመለከተ
የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ በቀጣናው ካሉ ሀገራት ጋር ሲነጻጻር ትንሽ ነው። ለአብነትም የአንድ ሊትር የነዳጅ ዋጋ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አንጻር
• ኬኒያ —-1 ነጥብ 7 ዶላር
• ጂቡቲ —-1 ነጥብ 77 ዶላር
• ኡጋንዳ —– 1 ነጥብ 57ዶላር
• ታንዛኒያ —– 1 ነጥብ 53 ዶላር
• ሩዋንዳ ——1 ነጥብ 99 ዶላር
• ኢትዮጵያ —–1ነጥብ 04 ዶላር
የኑሮ ጫናን በተመለከተ
መንግስት የነዳጅ ድጎማ ላይ ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ ነው። የእሁድ ገበያዎችም በስፋት እየተስፋፉ ነው። ማእድ ማጋረትን ጨምሮ ምርቶች በፍጥነት እንዲደርሱም የሎጂስቲክስ ፍሰትን ለማሳለት ከፍተኛ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
ሜጋ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ
የማዳበሪያ ፋብሪካ ከአንድ በላይ ፋብሪካዎችን በውስጡ የያዘ ነው። በድምሩ ከ3 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ፕሮጀክት ነው። ምንም የተለየ ችግር ካላገጠመን በቀር በተባለው ጊዜ የምናጠናቀቀው ይሆናል። የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያንም በርካቶች አትችሉም እያሉን እንችላለን የሚል የጸና አቋም አለን። ከወዲሁ አስቀድሜ የምነግራችሁ እንደ ቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ያለ ውስብስብና በዘመናዊ አስተዳደር የሚመራ ስራ አይቼ አላውቅም። የመጀመሪያውን ቦታውን የማዘጋጀት ስራውም በተያዘው ጊዜ የሚጠናቀቅ ይሆናል።

