በ2017 የበጀት ዓመት የ8 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚደረግ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀስላሴ ተናገሩ፡፡

ፕሬዚዳንቱ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክርቤቶች 4ኛ የሥራ ዘመን የጋራ ጉባኤ የመክፈቻ ንግግር ላይ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ በኢኮኖሚ ዘርፍ ከሚደረጉት ጥረቶች በታክስ መረቡ ያልገቡትን ወደታክስ መረቡ በማስገባትና አዳዲስ የታክስ ምንጮችን በማካተት አጠቃላይ የመንግስትን ገቢ 1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር ለማድረስ ይሰራል ብለዋል፡፡

ከታክስ የሚሰበሰበው ገቢ አጠቃላይ የሃገር ውስጥ ገቢ የሚኖረው ድርሻ 8 ነጥብ 3 በመቶ እንደሚደርስም ፕሬዚዳንት ታዬ አንስተዋል፡፡

መንግስት መደበኛ ወጪን በመቆጠብ ጥብቅ የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲን በመተግበር ፣የአምራች ዘርፉን በማጠናከር የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠርም ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነችበትን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ኢንቨስትመንት ተመራጭ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንቱ አንስተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ታዬ በዲፕሎማሲ፣በማህበራዊ፣የሰላምና ጸጥታ ዘርፎችም የመንግስትን ዝርዝር ዕቅዶች ለምክርቤቱ አባላት ያቀረቡ ሲሆን በተለይ የባህርበር ጉዳይ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ ሰጥቶ በመቀበል መርህ ተግባራዊ ለማድረግ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረምዋን አስታውሰዋል፡፡

Similar Posts