የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት

“በሞስኮ እየተካሄደ በሚገኘው 3ኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ በመገኘት መልዕክቴን ማስተላለፍ በመቻሌ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል። በዚህ ታሪካዊ መድረክ የምናሳልፋቸው ውሳኔዎች ተጨባጭ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የጋራ ቁርጠኝነት እና ትብብር እጅግ አስፈላጊ ነው።

ኢትዮጵያ ለዘላቂ ብልጽግናዋ እና ለሀገራዊ እድገቷ መሰረት በሆኑ ሶስት ቁልፍ ምሰሶዎች ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች ትገኛለች። እነዚህም በምግብ ዋስትና እና ምርታማነት፣ በአስተማማኝ የኃይል አቅርቦት፣ እንዲሁም በክህሎት እና በዕውቀት ሽግግር ላይ የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው።

የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ፣ በመከባበር እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የጸና ታሪካዊ ወዳጅነት ነው። ይህንን ወዳጅነት ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከሩሲያ ጋር በጋራ በመሆን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት የሚያስችሉ ተግባራትን በቁርጠኝነት እያከናወንን እንገኛለን። ይህ ስትራቴጂካዊ ትብብር የኃይል አማራጮቻችንን ከማስፋት ባለፈ የሀገራችንን የብልጽግና ጉዞ በእጅጉ የሚያፋጥን እንዲሁም የሁለቱ ሀገራት ትስስር ከምንጊዜውም በላይ የሚያጠናክር ይሆናል።”

Similar Posts